የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት እንደሚጀምር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት እንደሚጀምር አስታወቀ
ሰመራ፤ መስከረም 29 /2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን መለየት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ ዛሬ በሠመራ ከተማ በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የክልሉን ተወካዮች ለመምረጥ መድረክ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል።
በመድረኩ 432 ተባባሪ አካላት የሚሳተፉበትና ተወካዮቻቸው በብቃትና በገለልተኝነት እንዲመርጡ የሚመቻች መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በቀጣይ ምዕራፉ የተሳታፊዎች ልየታ በመምራትና በማስተባበር የሂደቱን ውጤታማነት እንደሚከታተል የገለጹት ዶክተር አይሮሪት፣ ከ48 ወረዳዎች የተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳ ለማሰባሰብ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ ብለዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ አመቺነት የሀገር የጎሳ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ሴቶች፣ወጣቶች፣የመንግሥት ሠራተኞች፣መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሂደቱ እንደሚሳተፉ ኮሚሽነሯ አመልክተው፤ ከየወረዳው 10 ሰዎች በአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት እንደሚወከሉ ተናግረዋል።
በተሳታፊ ልየታ ሂደት ላይ የጎሳ መሪዎችና ሐይማኖት አባቶች፣ የክልሉ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች፣የወረዳ ፍርድ ቤትና የሸሪዓ ፍርድ ቤት ዳኞች፣መምህራን ማህበር፣የወረዳ አስተዳዳሪዎች በተባባሪነት እንደሚሳተፉ አስረድተዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች ለሂደቱ መሳካት ይበጁኛል የሚሏቸውን ወኪሎች በተወካዮቻቸው አማካይነት እንዲያቀርቡ ዶክተር አይሮሪት ጥሪ አቅርበዋል።
ለተባባሪ አካላቱ ከነገ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት ስልጠና እንደሚሰጥም ተገልጿል።