500 ታማኝ ግብር ከፋዮች በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና  ሊሰጣቸው ነው- የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ የገቢዎች ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ500 ታማኝ ግብር ከፋዮች  ምስጋና እና ዕውቅና  ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።

5ኛውን ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የምስጋና እና ዕውቅና መርሐ-ግብርን በማስመልከት የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ እና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ከካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ "ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሀገራዊ የታክስ ህግ ተገዥነት ንቅናቄ በመካሄድ ላይ ነው።

የዚህ ንቅናቄ አካል የሆነው የታማኝ ግብር ከፋዮች ምስጋና እና ዕውቅና የመስጠት መርሐ ግብርም ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓም በብሔራዊ ቤተመንግስት ይከናወናል ብለዋል።

ሚኒስትሯ በመርሐ ግብሩም  በ2015 ዓ.ም በታክስና ጉምሩክ ህግ ተገዢነት እና በግብር አከፋፈል ሂደቱ ላይ የላቀ አፈፃፀም ያሳዩ 500 ግብር ከፋዮች እውቅና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ በተዘጋጁ የመለያ መስፈርቶች የተመረጡ 50 ግብር ከፋዮች በፕላቲኒዬም፣ 150 በወርቅ እና 300 በብር ደረጃ ምስጋና እና ዕውቅና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

በተጨማሪ  ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ያለማቋረጥ በፕላቲኒዬም ደረጃ ተሸላሚ የሆኑ 14 ግብር ከፋዮች በመርሐ ግብሩ  ልዩ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ሚኒስትሯ ተናግረዋል።


 

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ለእውቅናው የታጩ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለሀገር ንግድ እና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

በመርሐ ግበሩ እውቅና ከሚሰጣቸው መካከል ከዚህ ቀደም በታማኝነት ግብር ከፍለው እውቅና የተሰጣቸው  እና አዳዲስ ታማኝ ግብር ከፋዮችም እንዳሉበት ጠቅሰዋል።

ይህ መርሐ ግብር በራስ ተነሳሽነት ግብር የመክፈል ባህልን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ከ2011 ዓ.ም  ጀምሮ በየዓመቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ  ለታማኝ ግብር ከፋዮች የምስጋና እና ዕውቅና መርሐ ግብር በማካሄድ ላይ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም