ቀጥታ፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባለፉት ሦስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራትና የተገኙ ስኬቶችን ገመገመ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016(ኢዜአ)፦ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባለፉት ሦስት ወራት ያከናወናቸው ተግባራትን፣ የተገኙ ስኬቶችን እና ውስንነቶችን ገመገመ።

ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሃይማኖታዊ ሁነቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበሩ የጳጉሜን 6ቱን ቀናት ጨምሮ የአዲስ ዘመን መለወጫ፣ የመስቀል፣ የመውሊድ እና የኢሬቻ በዓላት እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴረሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባኤ መክፈቻ ሰላምና ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲከናወኑ በከፍተኛ ቅንጅት ትልቅ ሥራ መሠራቱን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ገልጿል።

በዚህም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ፕሮፌሽናል አቅሙን እየገነባ፤ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ትጥቆችን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ህግን በተከተለና ሥነ-ምግባርን በተላበሰ አኳሃን ውጤታማ የፀጥታ ሥራ ማከናወኑን በመግለጫው አመላክቷል።

ከዚህም በላይ በሀገራችን በተከበሩ ሁነቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል መዋቅር ጋር እንደ አንድ አካል ሆነው በትብብር አብሮ በመሥራት ለተገኘው ከፍተኛ ውጤት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡

በቀጣይ 100 ቀናት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ለይቶ የሀገራችን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንደሚሠራ የገለፀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ ወደፊትም በሀገራችን የሚከናወኑ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ከፀረ-ሰላም ኃይሎች እኩይ ተግባር ተጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ብሏል መግለጫው።

ግብረ-ኃይሉ ሥራዎቹን ተግባራዊ የሚያደርግበት ዕቅድ አዘጋጅቶ እስከታችኛው ፈፃሚ አካል ድረስ የሚያወርድ መሆኑን መግለጫው አመላክቷል።

ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ሥራ በተሳካ ሁኔታ እንዲተገበር የሕብረተሰቡ ተሳትፎ በተለመደው ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀረበው ግብረ-ኃይሉ ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት ተሳትፎውን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር እና የፀጥታና የደኅንነት አካላትን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አቅም በከፍተኛ ደረጃ የመገንባት ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሳውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም