ቀጥታ፡

የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሳድግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሳድግ ጠይቀዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አዲስ የተመረጡትን የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኤሚ ኢፖፕን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በዚህ ወቅትም ድርጅቱ ኢትዮጵያ ፍልሰትን ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን አዲሷ ተሿሚ ኤሚ ኢ. ፖፕ በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በነበራቸው ቆይታም የኢትዮጵያ መንግስት ከድርጅቱ ጋር ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር ያለውን ፍላጎት ገልጸውላቸዋል።

በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት አተገባበር ላይ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትም ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የሰፈራ እና የመልሶ ማቋቋም መርሐ-ግብር በመደገፍ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለው አፅንኦት ሰጥተዋል።

ኤሚ ኢ. ፖፕ በበኩላቸው የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን መጀመራቸው ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አክለውም ድርጅቱ ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው መልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ግንባታ መርሐ-ግብር አጋር ለመሆን ቁርጠኛ እንደሆነ መግለጻቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም