ቀጥታ፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የምርትና ምርታማነት ችግሮችን ለመፍታት በጥናትና ምርምር ማገዝ ይገባል - ኢንስቲትዩቱ

አዳማ ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቷ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች አካባቢ የሚታየውን የምርትና ምርታማነት ችግሮች ለመፍታት በጥናትና ምርምር ማገዝ  እንደሚገባ የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።

በሀገሪቷ  የሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ የሚስተዋለውን የሰው ሃይል ምርታማነት ክፍተቶች ለመሙላት ያለመ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጉታ ለገሰ በዚሁ ጊዜ ለኢዜአ እንደገለፁት የሲሚንቶን ምርታማነት ለማሳደግ የሰው ሃይሉ የስራ ባህል መለወጥ አለበት ብለዋል።

በፋብሪካዎች አካባቢ የምርትና ምርታማነት ዕድገት ማነቆዎችን ለመፍታት እንዲሁም የምርት ጥራትና ደረጃ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ችግር ፈች የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ዕውቀት መታጠቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የስልጠናው ዓላማም በተለይም የምርቱን አቅርቦት ለማሳደግና የአካባቢ ብክለትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የፋብሪካው የሰው ሃይል በቂ ክህሎትና ዕውቀት እንዲያገኝ ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የሲሚንቶ ዋጋን የአዋጭነት ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር መካሄዱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለምርታማነቱ ችግርና  ለምርቱ የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ የሆነበትን ምክንያቶችና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊሆኑ የሚችሉ ሂደቶች በጥናት መዳሰሳቸውን ተናግረዋል።

በሲሚንቶ ፋብሪካዎች አካባቢ የግብዓትና የመለዋወጫ ዕቃዎች ችግር መኖሩን የገለፁት ዶክተር ጉታ፤  በተጨማሪም የሰው ሃይል አደረጃጀትና የቅጥር ችግሮች በአንዳንድ ፋብሪካዎች ላይ እንደሚታይም መረጃዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪውን የስራ ባህል ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን ከማስተዋወቅ ባለፈ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ኢንስቲትዩቱ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ጉታ አክለውም በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባው የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ ሲጀምር በዓመት ከ1 ሚሊዮን  ቶን በላይ ሲሚንቶ እንደሚያመርት ጠቁመው፤ በዚህም አሁን ካለው አጠቃላይ የሲሚንቶ ምርት 1/4ኛውን ይዞ ወደ ገበያ ይገባል ብለዋል።

የፋብሪካው ግንባታ በመገባደድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በቅርቡ ስራ ይጀምራል ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሲሚንቶ፣ የሴራሚክስና  ሌሎች ማዕድናት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ስመኝ  ደጉ በበኩላቸው የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የሌሎች ማዕድን ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፉ የምርምርና ቴክኖሎጂ ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሲሚንቶ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሰው ሃይሉን በቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ ያሉትን ጉድለቶችና መልካም ተሞክሮዎችንም እንደ ግብዓት በመጠቀም ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ዳኜ አሰፋ እንደገለፁት ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር ቢኖርበትም በቀን 3ሺህ ቶን በሁለት ዩኒቶች እያመረተ ይገኛል ብለዋል።

በሲሚንቶ ፋብሪካ ግብዓት አቅርቦት ላይ ያለው መሻሻል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ያሉት አቶ ዳኜ፤ በተጨማሪ  የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት መፍታት ከተቻለ በሙሉ አቅማቸው በማምራት የሲሚንቶ ገበያን ማረጋገት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም