ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ህጎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራን አጠናክረን እንቀጥላለን-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የሚያወጣቸው ህጎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራን አጠናክረን እንቀጥላለን-የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 29/2016 (ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው ህጎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የምክር ቤቱ አባላት ገለጹ።
በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራሉ መንግሥት ሕጎችን የማውጣት ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል።
በንዑስ አንቀፅ 17 መሠረት ደግሞ ምክር ቤቱ ባወጣቸው አዋጆች መሰረት የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ስልጣን አለው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ በየዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችሉ ህጎችን በማውጣት ለህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈጻሚው ያስተላልፋል።
ያጸደቃቸው አዋጆች ተፈጻሚ እንዲሆኑም የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ስራዎችን ይሰራል ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ አባል መጋቢ ጥበባት አበረ አዳሙ፤ ባለፉት ዓመታት ምክር ቤቱ የጥላቻ ንግግር አዋጅን ጨምሮ በርካታ ህጎችን ማውጣቱን ተናግረዋል።
ይሁንና የህጎችን ተፈጻሚነት የመከታተል ስራ ክፍተቶች እንዳሉበት ገልጸው፤ በአዲሱ የስራ ዘመን የህጎችን አተገባበርና የአስፈጻሚውን አካል አሰራር የመቆጣጠር ስራን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ወርቅነሽ ጀማል፤ ሕግ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎችንና ፖሊሲዎችን በግልፅነትና ተጠያቂነት መርህ የመተግበርና የማስተግበር ሃላፊነት እንዳለበት ነው የገለጹት።
የምክር ቤት አባላትም ህጎች በአግባቡ ተፈጻሚ በማይሆኑበት ወቅት በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ተጠያቂነትን ለማስፈን ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።
ለዚህም የመስክ ምልከታና የሪፖርት ግመገማን በማጠናከር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲዘምን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነው ያነሱት።
ህግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የሚወጡ ህጎች ላይ ዜጎች ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለተግባራዊነቱ አጋዥ እንዲሆኑ የምክር ቤት አባላት አበክረን እንሰራለን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ምትክነሽ ጨለቀ ናቸው።
ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ዕጸገነት መንግስቱ፤ በምክር ቤቱ የሚወጡ ህጎች የዜጎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህ ባለፈም በህዝብ ደህንነት ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ህጎች ይወጣሉ ብለዋል።
ለአብነትም ከኢትዮጵያውያን መልካም እሴት ያፈነገጠ እና ግጭትን ሊቀሰቅስ የሚችል የጥላቻ ንግግር ላይ ቁጥጥር ለማድረግ አዋጅ መውጣቱን በማንሳት።
እንደዚህ ዓይነት አዋጆች ዋና ዓላማቸው ከፋፋይና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያስተጋቡ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ሁሉም ህብረተሰብ በተረጋጋ ሁኔታ በሀገር ልማትና ሰላም ላይ እንዲያተኩር መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በህዝብ አንድነትና ደህንነት ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ የወጡ ህጎችን ዓላማ ለማሳካት ምክር ቤቱ የግንዛቤ ስራዎችን ማስፋት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባላቱ አክለውም በኢትዮጵያ ለዘመናት የተከማቹ የመለያየትና የጥላቻ ትርክቶችን ወደ መግባባትና አንድነት ለማምጣት በዚህ ዓመት የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።