ቀጥታ፡

የእንግሊዝ የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ግሩፕን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2016(ኢዜአ)፦የእንግሊዝ የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ ዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን ጎብኝተዋል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና ሌሎች የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በቆይታቸውም የአየር መንገዱን የአቪዬሽን ዩንቨርሲቲና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከሉን ጉብኝተዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ ሶፊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው አገልግሎት ደስተኛ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል ነው ያሉት።    

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እንግሊዝ አገር መብረር ከጀመረ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ገልጸው ይህም ትስስር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።  

በዚህ ረገድ የዛሬው የእንግሊዝ የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ሶፊ ጉብኝት ፋይዳው የጎላ መሆኑን በመጠቆም። 

ጉብኝቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረውም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ በበኩላቸው የአፍሪካ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያን አየር መንገድ በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው አየር መንገዱ ስኬታማ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡም በእንግሊዝ ከተሞች መዳረሻ ከሆኑት መካከል ለንደን ጋትዊክ አዲስ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል።

ሶፊ ሄሌን ራይስ ጆንስ የእንግሊዝ ንጉስ ቻርለስ ሦስተኛ ታናሽ ወንድምና የስኮትላንድ ከተማ 'ኤዲንቦሮው' መስፍን ልዑል ኤድዋርድ ባለቤት ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም