የውጭ አገር የሥራ ሥምሪትን ለማሳለጥ የሚያስችል ብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድን ተቋቋመ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2016(ኢዜአ)፦ በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለልና ሥራዎቹን ለማሳለጥ የሚያስችል ብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድን መቋቋሙን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ። 

በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ ለዜጎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሰግድ ጌታቸው በዚሁ ጊዜ፤ ቡድኑ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪቱን ለማቀላጠፍ ታልሞ የተቋቋመ ነው ብለዋል።  

የቴክኒክ ሥራ ቡድኑ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ኤጀንሲዎች፣ ከአሰሪና ሠራተኛ ፌዴሬሽን የተውጣጣ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

የተቋቋመው ብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድን ኢትዮጵያዊያኖች በተለያዩ የሙያ መስኮች የውጭ የሥራ እድል እንዲያገኙ አበክሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያዊያኖች መብትና ጥቅም መከበር ላይም የሚሰራውን ሥራ ያጠናክራል ነው ያሉት።  

በዓለም ሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) በውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዋና የቴክኒክ አማካሪ አይዳ አወል በበኩላቸው ድርጅቱ ለቡድኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። 


 

በዚህም ኢትዮጵያዊያኖች በውጭ አገራት የተሻለ የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት። 

በ2015 በጀት ዓመት ከ102 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተው መሰማራታቸውን የተገለጸ ሲሆን ይህን አሃዝ በዘንድሮ ዓመት 500 ሺህ ለማድረስ ታቅዷል ተብሏል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም