በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የካይዘን ፍልስፍና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሻሻል ውጤት አምጥቷል- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/2016 (ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የካይዘን ፍልስፍና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሻሻል ውጤት ማምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።

የአፍሪካ ካይዘን ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

ጉባኤው "በመላው አፍሪካ የጥራትና ምርታማነት /በካይዘን/ ንቅናቄ እንዲስፋፋ የአፍሪካ ካይዘን ኢኒሼቲቭ አቅምን በማጎልበት የአህጉሩን የኢንዱስትሪና የኢኖቬሽን ጥረት ማገዝ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በኢትዮጵያ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ በመደረጉ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሻሻል ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን በመደገፍ ውጤት እንዲመዘገብ አግዟል ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የካይዘን የልህቀት ማዕከልን በመገደፍ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ለማስቻል እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።


 

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ፤ የካይዘን ፍልስፍናን በአግባቡ ስራ ላይ ያዋሉ ተቋማት ውጤታማና ከፍተኛ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

ይህም ዓለም ተወዳዳሪነት የሚጨምር በመሆኑ አፍሪካም ከዚህ የላቀ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲሉም ጠቁመዋል።

የካይዘን አሰራር በተለይም በአፍሪካ የቢዝነስ እንቅስቃሴ እንዲሻሻልና የህዝቦች ህይወት እንዲለወጥ እያገዘ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በጃፓን የተጀመረው የካይዘን አሰራር በአፍሪካ አገራትም ተግባራዊ በመሆኑ ለኢንዱስትሪ ዕድገት አስተዋጾ እያበረከተ ይገኛልም ነው ያሉት።

በአፍሪካ የእውቀት ሸግግር ለማድረግ በጃፓን መንግስት ድጋፍ በኢትዮጵያ የተገነባው የካይዘን የልህቀት ማእከል በይፋ ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

የካይዘን ፍልስፍና ምቹ የሆነ የስራ ቦታን መፍጠር፣ ብክነትን መቀነስ፣ ሀብትን በቁጠባና በአግባቡ መጠቀም፣ ጥራትን መጠበቅና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዝ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም