በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ጥቅል ሀገራዊ እድገት 7 ነጥብ 9 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28/2016 (ኢዜአ)፦ በ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ጥቅል ሀገራዊ እድገት 7 ነጥብ 9 በመቶ ለማድረስ እቅድ መያዙን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ መርኃ ግብር ተከናውኗል። 

በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የመንግስትን የ2016 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም 7 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች ጥረታችንን በማጎልበት አጠቃላይ የሀገራዊ እድገቱን 7 ነጥብ 9 በመቶ ለማድረስ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

ለአብነት በግብርናው ዘርፍ 22 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 810 ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ለመሰብሰብ ይሰራል ብለዋል፡፡

በዝቅተኛ ኢኮኖሚ የሚተዳደሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን እየተፈታተነ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ጥብቅ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ ገቢራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ተኪ ምርቶች ላይ በትኩረት በመሥራት የምርት አቅርቦቱ እንዲሻሻል ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ለ9 ነጥብ 15 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ በ2016 በጀት ዓመት ለ3 ነጥብ 05 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በአምስት ሀገራት ለ500 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ለመፍጠር መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም