በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው እድገት ኢትዮጵያ በለውጥ ምህዋር ውስጥ መሆኗን ማሳያ ነው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው እድገት ኢትዮጵያ በለውጥ ምህዋር ውስጥ መሆኗን ማሳያ ነው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2016 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገበው እድገት ኢትዮጵያ በለውጥ ምህዋር ውስጥ መሆኗን ማሳያ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ መርኃ ግብር ተከናውኗል።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የ2016 ዓ.ም ዋና ዋና የመንግሥት አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም፤ መንግሥት የ10 ዓመት የልማት እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ በመግባት በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ አስመዝግቧል ብለዋል።
ድኅነትና ኋላ ቀርነት ካለፈው ዘመን የወረስናቸው ስብራቶች ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ መንግሥት ችግሩን ከሥር መሰረቱ ለመቀየር የሚያስችል አገር በቀል የኢኮኖሚ አማራጭ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም 7 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ችግሮችን ወደ እድል መቀየር ተችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአዲስ እጥፋት ላይ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ ከነበረበት ቅርቃር በማውጣት በለውጥ ምህዋር ላይ እንዲጓዝ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
የብዝኃ ኢኮኖሚ አማራጮችን ገቢራዊ በማድረግ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እድገቱን በታቀደው ልክ ማስኬድ እንደተቻለም ገልጸዋል።
ለአብነት አገራዊ ጥቅል የሰብል ምርቱን ወደ 639 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ መቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።