የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሲቪል ግንባታ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዷል - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሲቪል ግንባታ በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዷል - ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ፤መስከረም 28/2016 (ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሲቪል ግንባታ በ2016 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ መታቀዱን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፤ የ2016 ዓ.ም ዋና ዋና የመንግሥት አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።
በ2015 ዓ.ም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አራተኛና የመጨረሻው ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነበትና የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ከ90 በመቶ በላይ የተሻገረበት መሆኑን ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ገልፀዋል።
የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን ለማብሰር ቁልፍ እንደሆነ በማመን ገንዘባችሁን፣ ላባችሁንና ድጋፋችሁን የሰጣችሁ ኢትዮጵያውያን የተገኘው ውጤት የእናንተ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በተያዘው ዓመት የግድቡ የሲቪል ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
"የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃብት ብቻ አይደለም" ያሉት ፕሬዝዳንቷ የቱሪዝምና የውሃ ኃብቶች በውስጡ የያዘና ለአካባቢ ጥበቃ አስዋጽዖ ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ግድቡ የሞራል ልዕልና የሕብረ-ብሔራዊነት እምርታም ሆኗል ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው የገለጹት።
የሕዳሴ ግድብ በጋራ ሀብቶቻችን ላይ የምናደርገው ልማት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥና የልማት ፍላጎታችንን የሚያሳካ ከመሆኑም አልፎ ለጎረቤት አገራትና የታችኛው የተፋሰስ አገራትን የማይጎዳ መሆኑ በተግባር ታይቷል ብለዋል።
በሁለቱም ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ መርሃ-ግብር የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።