ያሎ- አጎራባች ህዝቦችን ያገናኘና ያስተሳሰረው ገበያ - ኢዜአ አማርኛ
ያሎ- አጎራባች ህዝቦችን ያገናኘና ያስተሳሰረው ገበያ
በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ ዞን ግርጌ ላይ በሚገኘው ያሎ ወረዳ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ትልቅ ገበያ ይገኛል።
ያሎ ገበያ በገበያው ዙሪያ የሚኖሩት የአፋር፣ የአማራና የትግራይ ክልሎች ሕዝቦችን ለዓመታት ያስተሳሰረ ገበያ ነው።
በዕለተ ማክሰኞ በሚውለው ያሎ ገበያ የቁምና የቤት እንሰሳት፣ አልባሳት፣ እህልን ጨምሮ የተለያዩ ቁሶች ግብይት ይካሄድበታል።
ያሎ ገበያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በምሽት ጭምር ግብይት ሲከናወንበት የቆየ እንደነበርም ይነገራል።
በተለይ ከጅቡቲ የሚገቡ ኤሌክትሮኒክስና የተለያዩ አልባሳትን ከመገበያየት ባለፈ፤ ወደ ሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የማስተላለፊያ መሥመር ተደርጎ ይታይ እንደነበርም ተመልክቷል።
ገበያው ከሰሜን ዳሎል እስከ ፈንታሌ፣ ከጅቡቲ እሰከ አፋምቦ ድረስ በሚመጡ ገበያተኞች ይሞላል።
በተለይ የቻሉ በተሽከርካሪዎች፣ ያልቻሉ እስከ ሣምንት የሚደርስ የእግር ጉዞ አድርገው ይገበያዩበታል።
ለረጅም ዘመናት የህዝቦችን መስተጋብር አጠናክሮ የዘለቀው ይህ ገበያ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ እንደነበረ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሲገበያዩ ያገኘናቸው ገበያተኞች የገለጹ ሲሆን አሁን ግን በተፈጠረው ሰላም ገበያው ወደ ቀድሞ መመለሱን ተናግረዋል።
ከባላ አካባቢ የመጡት አቶ አሰፋ ኃይሌ ''ያገኘነው ሰላም ትልቅ ተስፋችን ሆኗል። አንድ ላይ እየዋልን ነው።በአሁኑ ጊዜ በሠላም እየተገበያየን፣እየሸጥን፣ እየገዛን ነው'' በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደአቶ አሰፋ ገለጻ፤ በአካባቢው ሰላም በመፈጠሩ የጎረቤታሞቹ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እየጎለበተ መጥቷል።
ውላጋ ከተባለ ቀበሌ የመጡት አቶ ብርሃኑ ተክሌ እንደተናገሩት በአካባቢው ገጥሞ የነበረው ችግር በመቃለሉ በሠላም መገበያየት እንደቻሉ ገልጸዋል።
ከቢሶ በር ከተማ የመጡት አቶ ደርቤ ሥዩም በገበያው ከአጎራባች ክልል ከሚመጡ ወገኖች ጋር በሰላም ግብይት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከአላማጣ ከተማ የመጡት አቶ ግርማዬ ደርቤ በአካባቢው የነበረው ችግር ተወግዶ በሰላም ግብይት መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
''የገበያው ድባብ የህዝብ አቀባበል እጅግ ደስ የሚል ነው። ይህ ግንኙነት እንዲቀጥልና ሰላማችን እንዲበዛና እንዲረጋገጥ ነው የምንፈልገው''ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ግብይት በአዲስ መልክ በመቀጠሉ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እያደገ መምጣቱን የያሎ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን መሐመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአፋር ክልል የንግድ ገበያ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት የማሰፈን ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ አብዶ ዓላ የያሎ ገበያ በክልሉ ከሚገኙት ገበያዎች ትልቁና በዕድሜ አንጋፋ መሆኑን መስክረዋል።
ቢሮው ከትግራይና አማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች ጋር የንግድ ሂደቱን የማሳለጥና የማረጋጋት ሥራዎች እያካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
ያሎ-የሦስት ክልሎች ሕዝቦችን አገናኝታና አገበያይታ ሣምንቱን በናፍቆትና በዝግጅት እንዲጠብቁ የምታደርገው የውሎ መድረክ።