ቀጥታ፡

ጽህፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ ከ5 ሺህ ለሚልቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ጂንካ ፤ መስከረም 28/2016(ኢዜአ)፦ የጂንካ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዝ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት በያዝነው አመት ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሩንም አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አያልነሽ አድሚ ለኢዜአ እንደገለፁት ጽህፈት ቤቱ በተያዘው በጀት አመት ከ5 ሺህ ለሚልቁ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገብቷል።

የሥራ ፈጠራው በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ትኩረቱን የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በበጀት አመቱ በአንደኛው ሩብ አመት ከ400 ለሚበልጡ ዕድሉ እንደተመቻቸና ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ጠቁመው በተለያየ ምክንያት የተፈጠረውን መዘግየት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በሥራ ዕድል ፈጠራው ዘርፍ የሚያጋጥሙ የማምረቻና የመሸጫ ሼድ ችግሮችን ለመቅረፍም 17 ሼዶች  መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል ።

ሌላው በተዘዋዋሪ ፈንድ የብድር አመላለስ መንጠባጠብ ምክንያት በብድር አቅርቦቱ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጽህፈት ቤቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ጽህፈት ቤቱ ለሥራ አጥ ወጣቶች ከሚያቀርበው የማምረቻና የመሸጫ ሼድ በተጨማሪ በዚህ አመት በከተማው ለተደራጁ 5 አምራች ማህበራት 1 ሺህ 700 ካሬ የማምረቻ ቦታ ድጋፍ ማድረጉን የጽህፈት ቤቱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ካሳሁን ገልጸዋል ።

በከተማው ለተደራጀው አንድ ዳቦ ማቀነባበሪያ ማህበር ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዘመናዊ የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ከልማት ባንክ ጋር በመሆን በ25 በመቶ የቅድመ ክፍያ በብድር መልክ ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

በከተማው የማሽነሪ ድጋፍ የተደረገለት የሁሴን ዳቦና ኬክ ማቀነባበሪያ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ወጣት ጌትነት ጥላሁን ማህበሩ ዳቦን በባህላዊ መንገድ  በመጋገር ለከተማው ነዋሪ ሲያቀርብ እንደነበር ጠቅሷል።

ሆኖም አሁን በልማት ባንክ የቀረበው የኤሌክትሪክ ዳቦ መጋገሪያ ማሽን በሰአት እስከ 1 ሺህ 500 ዳቦ መጋገር እንደሚያስችል ገልፆ በተመጣጣኝ የሃይል ፍጆታ እንዲሁም በውስን የሰው ኃይል ዳቦ በማምረት ለማከፋፈል ያስችላል ብሏል።

አስተዳደሩ ባደረገው ድጋፍ በሚፈልጉት የብሎኬት ማመረት ሥራ ለመሰማራት በማህበር መደራጀታቸውን የሚናገረው የ  "ጥረት ብሎኬት አምራች ማህበር'' ሰብሳቢ ወጣት ክያ ምስሌ በጂንካ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የክህሎት ስልጠና ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግሯል።

በተጠናቀቀው በጀት በከተማዋ ባለፈው ዓመት ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ከጂንካ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዝ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም