በዩኒቨርሲቲው የተከፈተው የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የላቀ እውቀት ይዘው እንዲወጡ እያደረገ ነው -ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28/2016(ኢዜአ)፦ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ሂሳብ የላቀ እውቀት ይዘው እንዲወጡ እያደረገ መሆኑን የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና ገለጹ።

የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ማጠናከር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ዓይነተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ 

ይህን ውጥን ከግብ ለማድረስም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በአቅራቢያቸው የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከመደገፍ ባለፈ ከታች ክፍል ጀምሮ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን ከፍተው በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ በአርዓያነት ይጠቀሳል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የራሱን የሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በመክፈት ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በማስተማር ሀገራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ 

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነ መስቀል ጠና ዩኒቨርሲቲው ከ2008 ጀምሮ የሳይንስና የሂሳብ ዝንባሌ ያላቸውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በመቀበል ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም ዩኒቨርሰቲው በቂ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎችን በመቋቋም ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን ሳይንስ በተግባር እንዲለማመዱ በማድረግ ውጤት ማምጣት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት ያስፈተናቸውን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ በማሳለፍ እውቅና ማግኘቱንም አንስተዋል፡፡



 

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ትውልድ ላይ በመስራት የጀመረውን በጎ ተግባር ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ወስደው ቢተገብሩት በርካታ ለአገር የሚጠቅሙ ዜጎችን ማፍራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የዩኒቨርሰቲ መምህራን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን በተወሰነ ጊዜ የሚያገኙበትና የሚያስተምሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ የሁለተኛ ደረጃ ልዩ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ወይም የክረምት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የሂሳብ ትምህርታዊ ስልጠናዎችን በማመቻቸት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የነገ የሀገር ጠቢብና ችግር ፈች ትውልድ እንዲሆኑ ማገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ በሚያስተዳድረው ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ህልማቸውን ለማሳካት ባገኙት ዕድል ጠንክረው በመማር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡    

የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ይኮሊያ ገረመው፤ ለስነ ህይወትና ለህክምና ሳይንስ ያላትን ዝንባሌ ለማሳካት መሰረት የሚጥል ትምህርት በመማር ላይ መሆኗን ተናግራለች።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ናሆም መስፍን በበኩሉ፤ የሚሰጡት ትምህርቶች በቤተ ሙከራ በተግባር ልምምድ የተደገፉ በመሆናቸው ጥሩ ዕውቀትን በመገብየት ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡


 

በተማሪዎች መካከል ያለው መተጋገዝና በጎ ፉክክርም እውቀትን ማሳደግ ላይ ያለው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚያገኙት አድማሰ ሰፊና ጥልቅ ትምህርት ነገ የሀገርን ችግር የምንፈታ እንድንሆን የሚያስችለን ነው ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ የባዮሎጂ መምህር የሆኑት ዳንኤል ሞኤሳ፤ ተማሪዎች ውጤትና እውቀት ተኮር በሆነ መንገድ እንዲማሩ ከማድረግ ባለፈ በስነ-ምግባርም ምስጉን እንዲሆኑ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የፊዚክስ መምህር የሆኑት መምህር ፌደሳ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን በንድፈ ሃሳብ ከማስተማር ባሻገር የተግባር ትምህርቶችንም በማሳየት ለውጤታማነታቸው በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

መምህራኑ አክለውም ትምህርት ቤቱ ዋነኛ የተግባር ሳይንስ ማዕከል በመሆኑ የተማሪዎች የፈጠራ ሀሳብ አፍላቂነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም