የፌስቱላ በሽታን ከማከም ባለፈ ለአካባቢው ሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ ነው- የመቱ ፌስቱላ ሕክምና ማዕከል - ኢዜአ አማርኛ
የፌስቱላ በሽታን ከማከም ባለፈ ለአካባቢው ሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ ነው- የመቱ ፌስቱላ ሕክምና ማዕከል
መቱ፤ መስከረም 28/2016 (ኢዜአ)፦ የመቱ ፌስቱላ ሕክምና ማዕከል የፌስቱላ በሽታን ከማከም ባለፈ ለአካባቢው ሕዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።
የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድማገኝ ክብረት፣ ፌስቱላ በወሊድ ላይ በሚያጋጥሙ ችግሮች፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሲፈጸም እና በሌሎች ምክንያቶች በሴቶች ላይ የሚደርስ የጤና እክል ሲሆን በሽታው ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮችን ያስከትላል ይላሉ።
ማዕከሉ በሽታውን ከማከም ባለፈ በበሽታው ምክንያት የሚደርሰውን ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ማዕከሉ የፌስቱላ በሽታ ላጋጠማቸው ሴቶችና እናቶች ከሚሰጠው ሕክምና ጎን ለጎን ችግሩን አስቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም "ዜሮ ፕሮጀክት" የተሰኘ ፌስቱላ ስለሚያስከትለው ችግር ዙሪያ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት እየተተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል።
"ዜሮ ፕሮጀክት" በኢሉባቦር ዞንና አካባቢው በፌስቱላ ምክንያት የሚያጋጥም የጤና ችግርን ለመቀነስ ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በተያዘው ዓመት ከ650 በላይ ለሚሆኑ የፌስቱላና ተያያዥ የጤና ችግሮች ላሉባቸው እናቶች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በማዕከሉ በሕክምና ሙያ የሚያገለግሉት ሲስተር ሕይወት ተስፋዬ፣ የበሽታው ተጠቂዎች የዕለት ዕለት ስራቸውን መከወን እንዳይችሉ ከማድረግ ባሻገር ለትልቅ የስነ-ልቦና ጉዳት የሚዳርጋቸው መሆኑን አስታውሰዋል።
ችግሩ የደረሰባቸው እናቶች በጊዜው አስፈላጊው ሕክምናና ክትትል ከተደረገላቸው በአጭር ጊዜ ሊድን የሚችል መሆኑን አንስተው ለዚህም አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በማዕከሉ በበሽታው በተለያየ ደረጃ የተጠቁ እናቶች የሚመጡ መሆኑን አንስተው እንደየችግሩ ደረጃ ከእስከ ቀዶ ሕክምና የሚደርስ ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጣቸውም ጠቁመዋል።
በማዕከሉ የ"ዜሮ ፕሮጀክት" ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ሀና ተስፋዬ፣ ፕሮጀክቱ በኢሉባቦር ዞን ወረዳዎች በፌስቱላ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠትን፣ ለችግሩ የተጋለጡትን የመለየት እንዲሁም ወደ ሕክምና ማዕከሉ መጥተው ህክምና እንዲያገኙ ማስቻል ነው።
ለስራው ስኬታማነትም በየቀበሌው ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ስልጠና በመስጠት የቤት ለቤት የግንዛቤ ማስጨበጥና የልየታ ስራው ውጤታማ እንዲሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በማዕከሉ በተሰጣቸው ሕክምና ለብዙ አመታት ከተቸገሩበት በሽታ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የተናገሩት የአሌ ወረዳ ነዋሪዎች ወይዘሮ መልኪቱ ረጋሳ እና ወይዘሮ እህታገኝ ተካ ናቸው።
ታካሚዎቹ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ባገኙት ሕክምና በአጭር ጊዜ ወደ ጤንነታቸው መመለስ እንደቻሉ ተናግረዋል
ወይዘሮ ባሪቱ መርዳሳ በአሁኑ ሰዓት በማዕከሉ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ እናቶች መካከል ሲሆኑ ወደ ማዕከሉ ሲመጡና አሁን በሚገኙበት ደረጃ መካከል ትልቅ ለውጥ መኖሩን አንስተው ከነበረባቸው ችግር የመውጣት ተስፋቸው እየለመለመ መሆኑን አንስተተዋል።
የመቱ ፌስቱላ ሕክምና ማዕከል በ2010 ዓ.ም. የተቋቋመና በምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ለፌስቱላ በሽታና ለማኅፀን መንሸራተት ችግር ለተጋለጡ እናቶች ሕክምና በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑም ተገልጿል።