ቀጥታ፡

የካይዘን ልህቀት ማዕከል በኢትዮጵያ መቋቋም በአፍሪካውያን መካከል የእውቀት ሸግግር እንዲኖር የጎላ ሚና አለው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2016 (ኢዜአ)፦ የካይዘን ልህቀት ማዕከል በኢትዮጵያ መቋቋም በአፍሪካውያን መካከል የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የካይዘን ልህቀት ማዕከል በዛሬው እለት ለምርቃት በቅቷል፡፡

በምርቃ ስነስርዓቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ ደመቀ በዚሁ ወቅት የካይዘን የልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያና በጃፓን መንግስት ትብብር በ 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት ግንባታ ላይ እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ ውጤታማ የሰው ሃብት ልማት በማሳለጥ እንደሀገር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

ልህቀት ማዕከሉ በኢትዮጵያ መቋቋሙ በአፍሪካውያን መካከል የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ሚናው ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ካይዘን ማለት እንደ አገርም ሆነ እንደ ግለሰብ የማያቋርጥ ለውጥ ማረጋገጥ ማለት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ፍልስፍናው በኢትዮጵያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ መሆን የጀመረው በፈረንጆች አቆጣጠር 2009 መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳድር ኢቶ ታካኮ ናቸው።

በፕሮግራሙ ላይም በግንባታ ሂደት ላይ የላቀ አፈጻጸም ለነበራቸው አካላት የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም