የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የውበት መገለጫና የአንድነታቸው ምልክት መሆኑን ተመልክተናል- ኬኒያዊያን የበዓሉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የውበት መገለጫና የአንድነታቸው ምልክት መሆኑን ተመልክተናል- ኬኒያዊያን የበዓሉ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2016 (ኢዜአ)፦ የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የውበት መገለጫና የአንድነታቸው ምልክት መሆኑን ተመልክተናል ሲሉ ኬኒያዊያን የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያና የኬኒያን ህዝብ ታሪካው ትስስር ለማጠናከር በኢሬቻ በዓል ላይ መታደማቸውን ጠቅሰው በተመለከቱት ድንቅ ትእይንት መደሰታቸውን ገልፀዋል።
የምስጋና፣ የይቅርታ፣ የሰላም እና የወንድማማችነት እሴቶች መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ለሁለት ተከታታይ ቀናት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በሆራ ፊንፊኔ ትናንት ከተከበረ በኋላ በዛሬው እለት ደግሞ ከማለዳ ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት በሆራ ሀርሰዲ ተከብሯል።
በበዓሉም ከጎረቤት ሀገር ኬኒያ የመጡ የሉዑካን ቡድን አባላት ከሶስት ቀናት በላይ በመጓዝ በበዓሉ ላይ ታድመዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ኬንያዊያን ተሳታፊዎች መካከል ዲዶ ጉራቾ፤ በዓሉን ለመታደም ለሶስት ቀናት በመጓዝ በስፍራው በመገኘት በማክበሩ መደሰቱን ገልጿል።
“ከኬንያ በመምጣት ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በጋራ በዓሉን ለማክበር ችለናል፤ የኢሬቻ በዓል አስደናቂ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ ተመልክተናል፤ ደስም ብሎናል” ብሏል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ዩሱፍ ዲባ፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አብሮነት ለመግለጽ በኢሬቻ በዓል ላይ መታደሙን ገልፆ በተመለከተው ሁሉ በእጅጉ መደሰቱን ተናግሯል።
በቆይታው ለተደረገለት መስተንግዶና አቀባበልም የላቀ ምስጋናውን አቅርቧል።
የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊያን የውበት መገለጫና የአንድነታቸው ምልክት መሆኑን ተመልክተናል ነው ያሉት ታዳሚዎቹ።
ሌላኛው የሉዑካን ቡድኑ አባል አብዲ ከሪም ሐጂ፤ በበዓሉ ላይ በቃላት የማይገለፅ ፍቅር ለማየት መብቃቱን በመግለፅ ይህንን ፍቅር በአብሮነት ልናስቀጥል ይገባል ብሏል።
የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያ እና የኬኒያን ህዝብ አንድነት እና የአብሮነት የሚያጠናክር መሆኑንም ሌላኛው ታዳሚ ሁሴን ዩሱፍ ገልጿል።
በቆይታው የአንድነት ማሳያዎችንና የፍቅር መገለጫዎችን ማየቱን ጠቅሶ ኢትዮጵያ ድንቅ ሀገር መሆኗን ተመልክቻለሁ ሲል ተናግሯል።