የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በሰላም ተጠናቋል- የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በሰላም ተጠናቋል- የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 27/2016(ኢዜአ)፡- የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል የገዳ ሥርዓት እሴቶችን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተከብሮ መጠናቁን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡
አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎችና ከጎረቤት ሀገራት የመጡ እንግዶች እና ቱሪስቶች የታደሙበት የ2016 ዓ.ም ሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የመጡ እንግዶችን በገዳ ሥርዓት እሴቶች መሠረት በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ ተቀብሏቸው በማስተናገድ ካከናወኑት ተግባር ባሻገር ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓልም ልክ እንደ የሆራ ፊንፊኔ ያለምንም የፀጥታ ችግር መከበሩን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገልጿል፡፡
ለበዓሉ በሰላም መከበር የድርሻቸውን ለተወጡ ለመላው የኦሮሞ ህዝብ፣ ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ለቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ ህዝብ፣ ለኦሮሞ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች፣ ለበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎችና ለወጣቶች በሙሉ ግብረ-ኃይሉ ምስጋና አቅርቧል፡፡
ለበዓሉ ፍፁም ሰላማዊነት ከዋዜማው ጀምረው እስከ በዓሉ ማጠናቀቂያ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ኃላፊነታቸውን በትጋትና በብቃት ለተወጡ መላው የፀጥታ ተቋማት አመራሮችና አባላትም የጋራ ግብረ-ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል፡፡