ሰላማችንን በማስጠበቅ እንደ ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላት የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ መስራት አለብን - የበዓሉ ተሳታፊ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሰላማችንን በማስጠበቅ እንደ ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላት የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ መስራት አለብን - የበዓሉ ተሳታፊ ወጣቶች
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 27/2016 (ኢዜአ)፦ ሰላማችንን በማስጠበቅ እንደ ኢሬቻ ያሉ የአደባባይ በዓላት የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ መስራት አለብን ሲሉ የሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ በዓል ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።
የሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ የአንድነትና የወንድማማችነት ዓርማ" በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ ተከብሯል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በበዓሉ ለመሳተፍ በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ የተገኙ ወጣቶች ኢሬቻ ወንድማማችነት በጉልህ የሚታይበት የምስጋና በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ የአደባባይ በዓላት አንዱ በሆነው የኢሬቻ በዓል ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን ድስታ ገልጸዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ ገቢኪያ ቀጀላ የኢሬቻን እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጿል።
ህዝብ በብዛት የሚሳተፍባቸው የአደባባይ በዓላት ከምንም በላይ ሰላም ይፈልጋሉ ብሏል።
በመሆኑም በተለይ ወጣቶች ሰላማችንን በማስጠበቅ የአደባባይ በዓላት የበለጠ የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባናል ነው ያለው።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ሂኮ ደንቦ በባህላዊ አልባሳት ደምቆ በመገኘት እና በሰላማዊ መንገድ ማክበር ይገባል ብላለች።
በዓሉ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆንም መስራት እንደሚገባና ለዚህም ወጣቱ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጻለች።
የበዓሉን እሴቶች ለጎብኚዎች ማስተዋወቅ ላይ በትኩረት በመስራት ረገድ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን መሳተፍ እንደሚጠበቅበትም ተናግራለች።
የበዓሉን ስርአት የሚያንጸባርቁ ስራዎችን በስፋት መስራት ይገባል ያለው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ግርማ መኮንን ነው።
ወጣቶች በመተባበር በተለይ የዓደባባይ በዓላት የበለጠ የጎብኚዎችን ቀልብ እንዲስቡ ማድረግ ይገባናል ብሏል።
መገናኛ ብዙሀንም ለዚህ ትልቅ አቅም መሆናቸውን ተናግሯል።
ወጣት ቤተልሄም ደየሶም በበኩሏ በዓሉ የአብሮነት እና የአንድነት መሆኑን በመግለጽ ይህንን እሴት ማስፋት እንደሚገባ ገልጻለች።
በኢሬቻ የሚንጸባረቁ ድንቅ አሴቶችን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን ወጣቶች ቀዳሚ ልንሆን ይገባል ብላለች።
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ተወካዮች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ትላንት በአዲስ አበባ በድምቀት መከበሩ ይታወሳል።