የበዓል አልባሳት ገበያ ሌላኛው የኢሬቻ ድምቀት - ኢዜአ አማርኛ
የበዓል አልባሳት ገበያ ሌላኛው የኢሬቻ ድምቀት
ኢሬቻ የኦሮሞ የገዳ ስርዓት መገለጫ ከሆኑት ወስጥ አንዱ ሲሆን፥ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በስፋት የሚከበር የባህልና እሴት መገለጫ የምስጋና በዓል ነው።
የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በድምቀት የተከበረ ሲሆን የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በአል ደግሞ በቢሾፍቱ ከተማ በነገው እለት ይከበራል።
የበዓሉ ዋዜማ በርካቶች በቢሾፍቱ ከተማ በመገኘት በድምቀት እያከበሩት ሲሆን ለበዓሉ ድምቀት ከሰጡት መካከል የበአል አልባሳት ገበያ ይገኝበታል። ኢዜአ ተዘዋውሮ ካነጋገራቸው የበዓል አልባሳት አቅራቢዎች መካከል ጸደቀ ደገፋ የተለያዩ አልባሳትን በመስራትና የተለያዩ ህትመቶችን በቲሸርቶች ላይ በማተም ለበዓሉ ታዳሚዎች እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።
በዓሉ ከጊዜ ወደጊዜ እየደመቀ እና እያማረ መምጣቱን እንዲሁም ገበያውም የበሉ አንዱ ድምቀት መሆኑን ገልጾ፤ በዓሉን ከማስተዋወቅ ባለፈም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንም እያገኘ መሆኑን ተናግሯል።
ሌላኛዋ የበዓል አልባሳት አቅራቢ ኦብሴ አለሙ የበዓል አልባሳቱ ገበያ የበዓሉ ትልቁ ድምቀት መሆኑን ተናግራለች።
የተለያዩ ባህሉን የሚገልጹ አልባሳት እንዲሁም ጌጣጌጦችን ለገበያ ማቅረቧን ገልጻለች።
በዓሉ ትልቅ የገበያ አጋጣሚ የፈጠረላት መሆኑን እና ሁሉም አቅሙ በፈቀደውና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዛቸው የሚችለው አልባሳት እና ጌጣጌጦችን ማቅረቧን ገልጻለች።
በግብይት ወቅት ያገኘነው ሽመልስ ፍቃዱ በበኩሉ የበዓል አልባሳትን በመረጡት ዲዛይን በስፋት ማግኘቱን ተናግሯል።
በገበያው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አልባሳት መመልከቱን ገልጾ ይህም የባህል ትስስርን እንደሚያጠናከር ገልጾ፤ በዓሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገቢ ምንጭ የሚፈጥር መሆኑን አስረድቷል።
ሌላኛዋ በግብይት ወቅት ያገኘናት ከባሌሮቤ የተገኘችው አለም ስለሺ ኢሬቻ በጉጉት የምንጠብቀው በአል ነው ብላለች።
በግብይቷም ለበዓሉ በተለያዩ አማራጮች የቀረቡ አልባሳትን ለመመልከት መቻሏን ገልጻለች። በዓሉን በይበልጥ ከሚያደምቁት ሁነቶች መካከልም የበዓል አልባሳት ገበያ አንዱ መሆኑንም ተናግራለች።
ወደከተማው ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ለተደረገላት አቀባበልም ምስጋና አቅርባለች።