የዚህ ዓመት የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ ልማት፣ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል - የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዚህ ዓመት የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ ልማት፣ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል - የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 26/2016(ኢዜአ)፦ የዚህ ዓመት የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ ልማት፣ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥና የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ሊሆን እንደሚገባ የተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የፊታችን ሰኞ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን በማብሰር በንግግር ይከፍታሉ። በዕለቱም የዚህ ዓመት የፌዴራል መንግስቱን ዓመታዊ ዕቅድ ትኩረት አቅጣጫ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢዜአ 6ኛው ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በማስመመልከት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አነጋግሯል። ዓመታዊ የመንግስት ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ "ምን ይሁን?" ሲልም ነዋሪዎችን ጠይቋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የአፋር ክልል፣ የጋምቤላ ከተማና የሀረረ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለልማት፣ ለሰላምና ደህንነት እውን መሆን መስራት ይጠበቅበታል።
ለዚህም የመንግስት የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ በልማት፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ላይ መሆን እንዳለበት ሀሳባቸውን አጋርተውናል።
አቶ አለሙ ሂርጳ እንዳሉት፤ የመንግስት ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት የአገሪቷ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ሕዝቡ ለተለያዩ ፈተናዎች እየተዳረገ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ ችግር የመጨረሻ እልባት አገኝቶ ዘላቂ ሰላም መስፈን አለበት ብለዋል።
በዚህ ዓመት ትልቅ ትኩረት እና እልባት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ልማትና የኑሮ ውድነት ማረጋጋት መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
በተለይም በአገሪቷ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በተጀመረው መልኩ በማስቀጠል የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት የሚያስችል ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩልም ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር የንግድ ስርዓቱን ወጥነት ባለው መልኩ እንዲተገበር መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አቶ አብዲ አህመድ እና ወይዘሮ አብዮት ተፈራ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ማረጋጋት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ሁሉም ዜጋ በአገሪቷ የልማት ስራ ውስጥ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች የበለጠ ማስፋትም ከመንግስት ስለሚጠበቅ በዓመታዊ እቅድ ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
''ሰላም ካለ ፍቅር አለ፣ ልማት፣ መከባበር አለ፣ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ለሰላም መስጠት'' ይገባል የሚሉት ደግሞ አቶ ኡጋላ ቺቢ ናቸው።
አቶ ኡጋላ እንደሚሉት፣ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም የአገሪቷ ህዝቦች ለመደማመጥ፣ ለመነጋገርና መግባባት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።
አቶ ዘርይሁን በቀለ በበኩላቸው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ያለው የኑሮ ውድነት ማረጋጋት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ቢሆን ብለዋል።
መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጀመራቸውን የልማት ስራዎች ወደ ሁሉም አካባቢዎች በማስፋት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ሌላው አቶ ሀቢብ መሓመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫ አንዱ መሆን ያለበት በማሕበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሰሩ አካላትን መቆጣጠር ነው።
በማሕበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ አሉታዊ መረጃዎች በሕዝቡ መካከል ፍርሃትንና ግጭትን እያባባሱ በመሆኑ መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።
አቶ አምሳሉ ቸኮልና አቶ መኳንንት በለጠም እንዲሁ ወጣቶች የትኛውም ፅንፍ ይዞ የሚንቀሳቀስ ኃይል መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
"ሰላምና መረጋጋት ያለ ህግ የበላይነት አይመጣም" ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሁሉም መተባበር እንደሚገባ ገልጸዋል።