የኢሬቻ በዓል አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የሰላም ምልክት ነው - አባ ገዳዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የሰላም ምልክት ነው - አባ ገዳዎች
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢሬቻ በዓል አብሮነትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር የሰላም ምልክት መሆኑን በሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የታደሙ አባ ገዳዎች ገለጹ።
የሆረ ፊንፊኔ በዓል አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የበዓሉ ታዳሚዎችም በባህል አልባሳት አምረውና ተውበው የአካባቢያቸውን ባህላዊ ጭፈራ በማሰማት በዓሉን በደስታ አሳልፈዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አባ ገዳዎች፤ የኢሬቻ በዓል የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም የምስጋና እና የወንድማማችነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።
አባ ገዳ ቆፋ ጎቤ እንደሚሉት፤ የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፋራ የሚሰጠው በሰላም ወጥቶ የመግባት የሰላም ምልክት ነው ብለዋል።
በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ በአደባባይ ወጥቶ ለፈጣሪ ምስጋና በሚያቀርብበት በኢሬቻ በዓል ላይም ጥላቻና ጸብን በማስወገድ ሰላማችን ማጽናት ይኖርብናል ብለዋል።
አባ ገዳ ተሬሳ አዳዲ በበኩላቸው ኢሬቻ ቂም፣ ጠብና ጥላቻ የሚወገድበት፤ አብሮነትና አንድነት የሚሰበክበት ህዝባዊ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ለአገር ሰላምና አንድነት በጋራ ጸሎትና ምስጋና የሚደረግበት የወንድማማችነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ የኢትዮጵያዊያንን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠናክር የአብሮነት መገለጫ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አባገዳ አህመድ አደም ናቸው፡፡
በዓሉ አንድነትና ሰላምን ለማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡