ኢሬቻ የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያና የጋራ የባህል ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠበቅ ይገባል- ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያና የጋራ የባህል ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠበቅ ይገባል- ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢሬቻ የመላ ኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያና የጋራ የባህል ሀብት በመሆኑ ትውፊቱን ጠብቆ ለሀገር ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና ማቅረቢያ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ሆረ ፊንፊኔ በድምቀት ተከብሯል፡፡
ከኢትዮጵያ የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጥተው በበዓሉ የተሳተፉ ዜጎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዘንድሮው ኢሬቻ ወንድማማችነትና አንድነት የተንጸባረቀበት በዓል ነው፡፡
አርቲስት መኩሪያ ባፋ ከወላይታ ዞን አርቲስት ሞዳ ሽዳ ደግሞ ከደቡብ ኦሞ ዞን የኢሬቻ በዓል ለማክበር አዲስ አበባ የመገኘታቸው ምክንያት በዓሉ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
የኢሬቻ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአደባባይ ከሚከበሩ የህዝብ በዓላት አንዱና የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበትና አብሮነታቸውን የሚያሳዩበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ኢሬቻ የኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት እንዲሁም የዓለም ቅርስ መሆኑን በመገንዘብ በጋራ ልናከብረውና በአንድነት ልናከብረው ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዓሉን ለመታደም ከሀዋሳ የመጡት አስናቀ አየለ፤ ኢሬቻ መነሻው ከኦሮሞ ህዝብ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመተሳሳብ እሴት ነው ብለዋል፡፡
ከጋሞ ዞን የመጡት ገነት ደመረ እና በርገኔ በቀለ እንዳሉት፤ ኢሬቻ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ያጠናክራል፡፡
የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴት በሚገልጽ መንገድ የሚከበር፣ ወንድማማችነትና ፍቅር የሚሰበክበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያን ቱሪዝም በማነቃቃት የዓለምን ጎብኝዎች ቀልብ በመሳብ የሀገርን ኢኮኖሚ ማገዝ የሚችል እሴት በመሆኑ በጋራ መጠበቅ ይገባናል ብለዋል፡፡