የሙስና መከላከል ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተቋማት በባለቤትነት እንዲመሩት እየተሰራ ነው - የፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የሙስና መከላከል ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተቋማት በባለቤትነት እንዲመሩት እየተሰራ ነው - የፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 25 /2016 (ኢዜአ)፦ የሙስና መከላከል ሥራውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተቋማት በባለቤትነት እንዲመሩት እየተሰራ መሆኑን የፌደራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።
ኮሚሽኑ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሙስና ሥጋት ጥናት ዙሪያ ከተቋሙ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሙስናና ብልሹ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው።
በኢትዮጵያም ሙስናና ብልሹ አሠራር የብሔራዊ ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ሙስናን የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች እየመጡ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
ለአብነትም በ2015 በጀት ዓመት በተደረገው የሙስና መከላከል ሥራ ብቻ 7 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እንዲሁም 1 ነጥብ 56 ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ መቻሉንም አንስተዋል።
በተያዘው 2016 በጀት ዓመትም በጥናት ላይ የተመሠረተ የሙስና መከላከል ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ በኮሚሽኑ 25 ዘርፎች ተለይተው የሙስና ሥጋት ጥናት እያካሄደ ነው ብለዋል።
አንዳንድ ተቋማትም ኮሚሽኑ የሚሰጠውን ግብረ-መልሶች እየተገበሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
እንዲያም ሆኖ ኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ሥራው ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ተቋማቱ በባለቤትነት እንዲመሩት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኮሚሽኑ በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ላይ በተደረገው የሙስና ሥጋት ጥናት በሚኒስቴሩ አንዳንድ ችግሮች መለየታቸውን ጠቁሟል።
በተለይም ፕሮጀክቶች በውል ጊዜያቸው ባለመጠናቀቃቸው ለተጨማሪ ዋጋ መጋለጥና የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ያለመስጠት ችግር እንዳለባቸው ተመላክቷል።
የኮሚሽኑ የኃብት ምዝገባና የጥቅም ግጭት ማስወገድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ መስፍን በላይነህ፤ ጥናቱን ባቀረቡበት ጊዜ እንደገለጹት፤ የሚኒስቴሩ ግዥ በዕቅድ ያለመመራትና የገበያ ጥናት ሳይካሄድ ግዥ መፈፀም ይስተዋላል።
ስለሆነም ተቋሙ እነዚህን ችግሮች መቅረፍና ግልፅ አሠራር መከተል እንዳለበትም አመላክተዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ የተሰጡ ግብረ- መልሶችን በመውሰድ ችግሮችን ለማቃለል ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም የድርጊት መርኃ-ግብር በማዘጋጀትም ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ይሁንና ከፕሮጀክት መጓተት ጋር ያሉ ችግሮች ሚኒስቴሩ በሚያስተዳድራቸው ፕሮጀክቶችና በሚመደብለት በጀት አለመመጣጠን የሚከሰት መሆኑን አንስተዋል።