ኢሬቻ የአገር ባህል ልብሶች የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ አድርጓል - የባህል ልብስ አቅራቢዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የአገር ባህል ልብሶች የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ አድርጓል - የባህል ልብስ አቅራቢዎች

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 25 /2016 (ኢዜአ)፦ኢሬቻ የአገር ባህል ልብሶች ምርትና ግብይት እንዲነቃቃ እድል መፍጠሩን ኢዜአ ያነጋገራቸው የባህል ልብስ አቅራቢዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን በአደባባይ በዓላት እና በሌሎችም ዝግጅቶች ላይ የአገር ባህል ልብሶችን የመልበስ ልምዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡
የባህል ልብስ ከሚዘወተርባቸው የአደባባይ በዓላት መካከልም መስቀል፣ ኢሬቻ፣ አሸንድዬ፣ አሸንዳ፣ ፍቼ ጫምባላላና ጥምቀት ለአብነት ይጠቀሳሉ።
አሁን አሁን ኢትዮጵያዊያን በእነዚህ በዓላት ላይ በአገር ባህል ልብስ ተውበው የበዓላቱን ስነ ስርዓት ሲያከናውኑ ማየት እየተለመደ መጥቷል።
በባህል ልብስ ምርት እና ግብይት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ወይዘሮ አባይነሽ መለስ ለዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የበርካታ አካባቢ የባህል ልብሶችን በማዘጋጀት ለገበያ ማቅረባቸውን ይገልጻሉ።
ልብሶቹ ባህላዊ ትውፊቶችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ገቢ በማግኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድሆን አስችሎኛል ብለዋል።
ሌላኛው በባህል ልብስ ምርትና ንግድ ላይ የተሰማሩት ባህሩ ከተማ በበኩላቸው፤ በርከት ያሉ ግለሰቦች ለበዓሉ የሚሆን የባህል ልብስ እየገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሕዝቡ ከባህል ወቅቶች ውጪም አገር ባህል ልብሶችን የመልበስ ልምድ ማዳበር እንዳለበትም ተናግሯል፡፡
ሌላኛዋ በዘርፉ የተሰማራችው ትዕግስት ብርሃኑ ከገበያ ባለፈ የባህል ልብሶችን እያስተዋወቀች እንደምትገኝ ገልጻለች።
ኢትዮጵያውያን የባህል ልብሶችን የመጠቀም ባህላቸው ማደግ ለስራ እድል ፈጠራ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግራለች።
የኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና በዓል የሆነው ኢሬቻ "የወንድማማችነትና የአንድነት አርማ" በሚል መሪ ሀሳብ ነገ በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ ከነገ በስቲያ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ይከበራል።