ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ በማደራጀት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 25 /2016 (ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አገር አቀፍ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ በማደራጀት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥምምነት ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ወክለው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሤና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ ፈርመውታል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ፤ በኢትዮጵያ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተበታተኑ በመሆናቸው በትስስር ለመሥራት መረጃው አስፈላጊ ነው ብለዋል። 

የሚደራጀው መረጃ መንግሥት የሚያቀርበውን መሠረተ-ልማት ጥራት ያለው ተደራሽና የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የሚደግፍ እንዲሆን ለማድረግ መሆኑን አመላክተዋል። 

ይህም ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ማበረታቻዎች ለታለመላቸው ዓላማዎች መዋላቸውን ለማረጋገጥና የኃብት ብክነትን ለመቀነስ የተደራጀ መረጃ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በከር ሻሌ በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያስጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እውን እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ለውሳኔ ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚያስችል ተዓማኒና ወቅታዊ መረጃ በማቅረብ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም