በአዳማ  የተመለከትነው ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ  የሚበረታታና ልምድ የሚወሰድበት ነው - የአፍሪካ ከንቲባዎች ሊደርሽፕ ኢንሼቲቭ ሉኡካን አባል

አዳማ፤ መስከረም 25 /2016 (ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ የተመለከቱት  ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥና አሰራር  የሚበረታታና   ልምድ የሚወሰድበት  መሆኑን  የአፍሪካ ከንቲባዎች ሊደርሽፕ ኢንሼቲቭ ሉኡካን አባል ገለጹ።

የሉኡካኑ አባላት በአዳማ የቴክኖሎጂ ማዕከልን ጨምሮ የተለያዩ የአገልግሎትና መሰረተ ልማት አውታሮችን ጎብኝተዋል።

የኢንሼቲቩ ሉኡካን አባልና በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ከተሞች ማዕከል አስተባባሪ ፕሮፌሰር ኢድገሪ ፓትረስ፤ አዳማ ከተማ በቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራር የተደገፈ ፈጣን ዕድገት ላይ መሆኗን መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል። 
 

በተለይ ከተማዋ ያላትን የመሬት ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደር ተግባራዊ ያደረገችው ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር "ካዳስተር" ስርዓትና የአገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በማድረግ ወደ ዲጂታል ለመቀየር እየተከናወነ ያለው ስራ  አበረታች ተሞክሮና ልምድ የሚወሰድበት  መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት እውን እንዲሆን ፣የሰው ሃይሉንና ውስን ሀብቱን በማቀናጀት የከተማዋ ገቢ ከማሳደግ  አንፃር ውጤታማ ስራ እንዳለ ለመገንዘብ እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

አዳማ ከተማ በኬፕታውን የአፍሪካ ከንቲባዎች ሊደርሽፕ ኢንሼቲቭ ላይ ያቀረበችውን ግቦች ማሳካት የሚያስችል ጉዞ ላይ መሆኑዋን በጉብኝታቸው መመልከታቸውንም አስረድተዋል።
 

የአፍሪካ ከንቲባዎች ሊደርሽፕ ኢንሼቲቭ አዳማ ከተማ የጀመረቻቸውን ዲጂታላይዝ አገልግሎትና ዕድገት እንዲሳካ ባለው ቴክኖሎጂና ዕውቀት ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን በበኩላቸው፤ አዳማ ከተማ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ረገድ አበረታች ውጤት እያመጣች መሆኗን ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሞደርናይዜሽን ለሌሎችም የሀገሪቱ  ከተሞች ትልቅ ተሞክሮና ልምድ የሚቀሰምበት ነው ብለዋል። 

በአፍሪካ ከንቲባዎች ሊደርሸፕ ኢንሼቲቭ እየተሳተፉ ያሉት ከተሞች አዳማና  አዲስ አበባ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሂደት በማዘጋጃ ቤት የሚተዳደሩ ከ250 በላይ ከተሞች በኢንሼቲቩ ተካተው ልምድ እንዲቀስሙ ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል።
 

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ ፤ አስተዳድሩ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዳዲስ አሰራርና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ከ33 ነጥብ 4 ሄክታር በላይ በህገ ወጥ የተያዘ መሬት ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የከተማውን ገቢ በማሳደግ  ወደ 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ማድረስ መቻሉን ያመለከቱት ከንቲባው ፤በዘንድሮው ዓመት 13 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅደን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል።

በተመሳሳይ ከ490 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች የወረቀት ፋይል ወደ ዲጂታል በመቀየር  የተሻለ ፈጣን አገልግሎት መስጠት የቻልንበትና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታን መፍታት የቻልንበት ነው ሲሉም  አመላክተዋል።

የከተማዋ  አስተዳደር የአሰራር ስርዓት ለማዘመንና ስማርት ማህበረሰብ ለመፍጠር ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፣ከኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲና ከሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥናትና ምርምር ላይ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም