ቀጥታ፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

ነቀምት ፤ መስከረም 25/2016 (ኢዜአ)፡-  በምስራቅ ወለጋ ዞን በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በዞኑ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ መዝጊያና በስራው የተሳተፉ አካላት እውቅና መስጫ መርሃ ግብር ተካሄዷል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው ታከለ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በክረምቱ  ለአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት፣ የመሸጋገሪያ ድልድዮች ጥገና፣ የገጠር መንገድ ግንባታ ተከናውኗል።

በተጨማሪም የደም ልገሳ፣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ማሰባሰብና የከተማ ጽዳትና ውበትም በክረምቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ናቸው ብለዋል።

በበጎ አድራጎት ስራው ወጣቶችን በመቀስቀስ 448 አዳዲስ የአቅመ ደካማ እናቶች የመኖሪያ ቤት ግንባታ የቤት እድሳት መከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም ይወጣ የነበረ 80 ሚሊዮን የመንግስት በጀት ለማስቀረት ታቅዶ 100 ሚሊየን ገንዘብ ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

በተሰራው ስራም ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

በዞኑ የሌቃ ዱለቻ ወረዳ የስፖርት እና ወጣቶች ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ድንበሩ ግርማ በወረዳው 12 ሺህ 171 ወጣቶችን ያሳተፈ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።

በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገለት ተማሪ አንበሴ ተክሉ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ባገኘው ድጋፍ ትምህርቱን ጠንክሮ ለመማር መዘጋጀቱን ገልጿል።


 

የአረጆ ወረዳ ነዋሪው አቶ ታምሩ ሹና በበኩላቸው በጉልበት ስራ ሰባት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ ገልፀው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተለያየ ዓይነት ድጋፍ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ጠቁመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ለስራው ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም