ቀጥታ፡

የአባገዳ ባንዲራ ቀለማት እና የቀለማቱ አቀማመጥ ትርጉም

የአባገዳ ባንዲራ ቀለማት አቀማመጥ ከላይ ወደ ታች ጥቁር፣ ቀይ፣ ነጭ ነው።

ጥቁር መደብ፦

የፈጣሪ የበላይ መሆንን የሚገልጽ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ራሱ ጥቁር እንደሆነው ሁሉ ፈጣሪው /ዋቃ/ (እግዚአብሔር) ጥቁር ነው ብሎ ያምናል። ጥቁር ቀለምም በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የቀዳሚነት መገለጫ ነው። ጥቁሩ ፈጣሪ ያለው ከላይ ነው፤ ዝናብ የሚዘንበው ከላይ ባለው ጥቁር ደመና ነው፣ ራሳችን ላይ ያለው ፀጉር እስኪሸብት ድረስ ጥቁር ነው፤ የዓይናችን ብሌን ጥቁር ነው - የሚገኘውም ከላይ ነው። እናም ጥቁር ቀዳሚ የመሆን መገለጫ ነው።

ቀይ መደብ፦

የብቃት፣ ብስል የመሆን፣ ሙሉ ሆኖ የመገኘት እና ለሕዝብ ነፃነት መሥዋዕት የመሆን መገለጫ ነው። ሁሉም ነገር በጊዜው ሙሉ ሆኖ የመገኘት ምሳሌ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ነገር የብቃት ደረጃው ላይ መድረሱን ሲገልጽ “diimate” /ቀላ/ ብሎ ይገልጻል።

ነጭ መደብ፦

የነገሮች ፍፃሜ መገለጫ ነው። እንደ ምሳሌ፦ ጠቁሮ ዝናብ የሚሰጠን ደመና ነጭ ሲሆን አይዘንብም ማለት ነው፤ ጥቁር የነበረው የሰው ፀጉር እርጅና ሲደርስ ይሸብታል (ነጭ ይሆናል)፣ ነዶ ያለቀ እንጨት አመዱ ነጭ ነው … ስለዚህ ነጭ የፍፃሜ መገለጫ ነው ብሎ ያምናል - የኦሮሞ ሕዝብ።

(ኢቢሲ)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም