ኢሬቻ የአብሮነት ማሰሪያ ሐረግ - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የአብሮነት ማሰሪያ ሐረግ
ኢሬቻ የአብሮነት ማሰሪያ ሐረግ
(አሸናፊ በድዬ)
ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነው፤ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት።
ስለ ሰላምና አንድነት የሚዘመርበት፣ ስለመጪው ጊዜ መልካም ምኞት የሚገለጥበት፣ ሁሉን ላደረገ ፈጣሪ ምስጋና የሚቸርበት የአብሮነት በዓል ነው።
በልመናው፣ በምርቃቱ፣ በምስጋናው ሁሉ ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን! አሜን! አሜን!) የሚሉ ድምፆች ይስተጋባሉ።
"ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!
ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ሁሉ ጠብቀን!
ለምድራችን ሰላም ስጥ!
ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!
ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!
ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!" በማለት ይመረቃል። ሕዝቡም ይሁንልን ይደረግልን ሲል "ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!" ይላል።
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም በማግስቱ እሑድ መስከረም 27 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ ይከበራል።
የክራምት ወራት እንዳበቃ የሚከበረው "ኢሬቻ መልካ" (በውሃ ዳርቻ የሚከበር) ሲሆን በዓመቱ አጋማሽ ላይ የሚከበረው "ኢሬቻ ቱሉ" ደግሞ በተራራማ ቦታ የሚከበር ነው።
ኢሬቻ መልካ የሚከበረው በመስከረም ወር ከመስቀል በዓል በኋላ ሲሆን፤ የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ምስጋና የሚቀርብበት ነው።
ኢሬቻ ቱሉ የሚከበረው የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። በዚህም ፈጣሪ ''እርጥበት አትንፈገን፣ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡ፤ የዝናብ ንፋስ ስጠን'' በማለት ለፈጣሪ ተማጽኖ የሚቀርብበት ነው።
"ይህን ተራራ የፈጠርክ ፈጣሪ ወቅቱን የሰላም አድርግልን፣ የሰላም ዝናብ አዝንብልን፣ ጎርፍን ያዝልን፣ የተዘራው ፍሬ እንዲያፈራ እንለምንሃለን" እያለ በኢሬቻ ቱሉ ላይ ፈጣሪውን ይለምናል፡፡
በኢሬቻ በዓል የፈጣሪ ምህረት፣ ዕርቅ፣ እዝነት እና በዓሉ የሰላም በዓል እንዲሆን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ኦሮሞ ፈጣሪውን ይጠይቃል፤ ይማፀናል፤ ለተደረገለትም ነገር ሁሉ ያመሰግናል።
የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን፤ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለዘመናት ሲከበር የቆየ በዓል ነው።
በዓሉ በዋናነት በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ፤ በቢሾፍቱ ከተማ በሆራ ሀርሰዲ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ታድሞ የሚከበር ቢሆንም በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች በድምቀት ይከበራል።
የኦሮሞ ሕዝብ ምድርን እና ሰማይን ለፈጠረው ፈጣሪ "ዋቃ" ምስጋናውን ለማድረስ የኢሬቻ በዓልን ያከብራል ይላሉ አባገዳዎች።
የኦሮሞ ሕዝብ በዕድሜ ልዩነት ሳይገደብ የኢሬቻ በዓልን ለዘመናት በጋራ፣ በአንድነትና በፍቅር ሲያከብር ቆይቷል።
በዝናባማው የክረምት ወቅት በጅረቶችና ወንዞች መሙላት ምክንያት ተራርቆ የቆየው ዘመድ አዝማድ በኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ሥፍራ ይገናኛል፤ ይጠያየቃል፤ ናፍቆቱንም ይወጣል።
አባቶች ክረምት በለሊት ይመሰላል ይላሉ። ለሊት ደግሞ ጨለማ ነው። ጨለማው ሲነጋ ደግሞ ብርሃን ነው፤ ብርሃን ደግሞ ውበት ነው፤ መታያና መድመቂያም ነው።
ለዚህ ነው በኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ሁሉም ውብ የባህል ልብሱን በመልበስ በደስታ በዓሉን ለማክበር የሚመጣው።
ሕዝቡ በዓሉ ወደሚከበርበት ሥፍራ የሚሄደው በተናጠል ሳይሆን በሕብረትና በአንድነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢሬቻ የአንድነትና የአብሮነት በዓል ነው የሚባለው።
በኢሬቻ ልዩነት የለም፤ ፀብ የለም፤ ክፋት የለም፤ ይልቁንም ምስጋና ይጎርፋል፤ ፍቅር ይሰፍናል፤ አብሮነት ያብባል።
ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላምና የአብሮነት ምልክት ሲሆን፤ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚወጣው ታዳሚም እንደ እርጥብ ሣር ወይም አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ የበዓሉን ስነ-ስርዓት ያከናውናል።
ይህን የሚያደርገውም "ፈጣሪያችን ሆይ አንተ ያፀደቅከው ነው አብቦ ፍሬ ያፈራው፤ ለዚህም እናመሰግንሃለን" በማለት የፈጣሪን መልካምነት ለማሳየት ነው።
በሌላ በኩል እርጥብ ሣር የልምላሜ ምልክት በመሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫም ጭምር በመሆኑ ነው በኢሬቻ በዓል እርጥብ ሣር የሚያዘው።
የኦሮሞ ሕዝብ ለሰላም ትልቅ ሥፍራ ይሰጣል። ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ ብሎም ያምናል። በምርቃቱም "ቡና ፊ ነጋአ ሂንደቢና" ብሎ ይመራረቃል። ቡናና ሰላም አያሳጣችሁ ማለት ነው።
ለዚህም ነው በኢሬቻ በዓል ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደኅንነት ፈጣሪ የሚለመነው። ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ፀሎት እንዲሉ አበው በኢሬቻ የተጣላ ታርቆ፣ ቂሙን ረስቶ በንጹህ ልቦና ፈጣሪ ንጹህ ወዳደረገው የውሃ አካል ይሄዳል፤ በዚያም ፈጣሪውን ያመሰግናል።
የኢሬቻ በዓል ሲከበር ከሚከወኑ ሥርዓቶች መካከል ሴቶች ሲቄ፣ እርጥብ ሣር እንዲሁም ጮጮ ይዘው ከፊት ሲመሩ አባ ገዳዎች ደግሞ ቦኩ፣ አለንጌ እና ሌሎችንም በበዓሉ ሥርዓት የሚፈቀዱትን ሁሉ በመያዝ ወደ ሥርዓቱ አከባበር ያመራሉ።
ኦ ያ መሬሆ…………………መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ ኡማ ሁንዳ መሬሆ…………………ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ ለፋ ኡምቴ መሬሆ………………… ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ
ያ ዋቃ መልካ ኡምቴ መሬሆ………………… ያ መሬሆ
መሬሆ………………… መሬሆ እያሉ ያመራሉ።
የሁሉ ፈጣሪ፣ ምድርን የፈጠርክ፣ ወንዙን የፈጠርክ . . . ምስጋና ለአንተ ይሁን በማለት ያመሰግናሉ፤ ይዘምራሉ።
የኢሬቻ በዓል ሥነ-ሥርዓት በአባመልካ ተከፍቶ በአባ ገዳዎች ተመርቆ ከተጀመረ በኋላ መላው ሕዝብ በአንድነት ሥርዓቱን ያከናውናል።
ኢሬቻ ሁሉም በጋራ የሚያከብረው፣ የሁሉም ማጌጫ፣ መድመቂያ እና የአብሮነት መገለጫ ነው።
ብሔር ብሔረሰቦች የሚታወቁበትን ባህላዊ ልብስ በመልበስ በቋንቋቸው ፈጣሪን እያመሰገኑ በዓሉን በአንድነት ያከብራሉ። ለዚህም ነው ኢሬቻ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን በዓልና መገለጫ ነው የሚባለው።
በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ ሀርሰዲ በዓላት ላይ ለመታደም ወደ አገር ቤት ይመጣሉ። የውጭ አገራት ጎብኚዎችና እንግዶችም በትዕይንቱ ይታደማሉ።
ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት ከኬንያ አገር የመጡ ልዑካን በዚህ በዓል ላይ በመታደም የበዓሉን ትልቅነት እና የኢትዮጵያውያን የአብሮነት መገለጫ መሆኑን መመስከራቸው ይታወሳል።
በዚህ ዓመትም የሦስት ጎረቤት አገራት ልዑካን በዚህ በዓል ላይ እንደሚታደሙ የተገለጸ ሲሆን፤ የኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ታንዛኒያ አገራት ተወካዮች እንደሚታደሙ ይጠበቃል።
አያሌ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ያሉት ይህ የምስጋና በዓል እውነተኛ ወንድማማችነት የሚታይበት፣ አንድነት የሚጎላበት፣ አብሮነት የሚጠናከርበት፣ ሰላምና ተስፋ የሚታወጅበት ትልቅ አገራዊ እሴት ነው።
በባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ ባህላዊ ምግቦችና ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችና ተቋማት ኢሬቻና መሰል የአደባባይ በዓላትን እንደመልካም የገበያ አማራጭ ይጠቀሙባቸዋል።
ኢሬቻ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁሶች በስፋት የሚተዋወቁበት ታላቅ መድረክ ነው። በእርግጥም ይህንን ውብ የጋራ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል ነውና በምስጋና እንደጀመርን በምስጋናና ምርቃት እንሰነባበት።
"ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ!
ከመጥፎ ነገር ጠብቀን!
ንጹህ ዝናብ አዝንብልን!
ከእርግማን ሁሉ አርቀን!
እውነትን ትቶ ከሚዋሽ አርቀን!
ከረሃብ ሰውረን!
ከበሽታ ሰውረን!
ከጦርነት ሰውረን!
ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን! አሜን! አሜን!)