ቀጥታ፡

ለስደተኞች የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 25 /2016 (ኢዜአ)፦ ለስደተኞች የዲጂታል ፋይዳ መታወቂያ ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ዛሬ በሶስት ተቋማት መካከል ተፈርሟል። 

ምምነቱን የተፈራረሙት የኢፌዴሪ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ናቸው።

የኢፌዴሪ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን በዚሁ ወቅት በስምምነቱ አማካኝነት ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በዲጂታል መታወቂያው በኢትዮጵያ የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ይህም ኢትዮጵያ ለስደተኞች ጥቅም የሚሰጡ መብቶችን ተግባራዊ እያረገች ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮዳሔ ዘሚካኤል፤ በስምምነቱ መሰረት ተቋማቱ የጋራ የመረጃ ልውውጥ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ያላትን በጎ አመለካከትና ተቀባይነት የሚያሳይ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የኢትዮጵያ ተወካይ አንድሪው ምቦጎሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረችው የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ስደተኞች ማንነታቸው ተረጋገጦ የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑም ትልቅ ጅማሮ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሙከራ ትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በ2015 ዓ.ም የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

እስከ አሁንም ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ብሔራዊ መታወቂያ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ምዝገባ ተደርጓል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 90 ሚሊየን ዜጎችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እቅዱ የተፈናቀሉ ዜጎች፣ ሰብአዊ እርዳታ የሚያሻቸውና ሌሎች ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ማቅረብ የማይችሉ ዜጎችን ታሳቢ ማድረጉም ተነግሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም