ቀጥታ፡

መንግሥት በዓመቱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል- የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2016 (ኢዜአ)፦ መንግሥት በአዲሱ የ2016 የስራ ዘመን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የስራ ዘመናቸውን በመጪው ሰኞ መስከረም 28/2016 በይፋ ይጀምራሉ።

በዕለቱም የምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስነ-ስርዓት የሚደረግ ሲሆን፤ መንግስት በ2016 ዓ.ም ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን ጉዳዮች የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ለህዝብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች መንግስት በ2016 ዕቅዱ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዘርፌ ፍቅሩ፤ ሀገር ፀንታ እንድትቆም ዘላቂ  ሰላም ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ መንግሥት የጀመረውን ህግ የማስከበርና ሰላም የማስፈን ተግባር በአጽንኦት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።


 

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች አባላትም በሚያደርጓቸው ውይይቶች ህግ አስፈጻሚ ተቋማት ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንዲሰጡ የመፍትሔ አቅጣጫ ማመላከት አለባቸው ነው ያሉት።

ህዝብን ያሳተፈና በውይይት ችግሮችን መፍታትን ማዕከል ያደረገ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የምክር ቤት አባላትና የመንግስት ትኩረት መሆን እንደሚገባው አስረድተዋል።

የኑሮ ውድነትን እያባባሱ የሚገኙ ችግሮችን ለመቅረፍና የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ የዋጋ ማረጋጊያ መፍትሔዎችም እንዲተገበሩ ጠይቀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አለማየሁ ግርማ  በበኩላቸው፤ ዜጎች የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚ ተቋማትን መጠየቅና ማገዝ አለባቸው ብለዋል።


 

የህዝብ ተመራጮች የተሰጣቸውን ውክልና በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል የህዝብ ጥያቄዎች እንዲፈቱ የበኩላቸውን ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

መንግሥት  ለበጀት ዓመቱ በምክር ቤት ያፀደቀውን በጀት የሀገርና የህዝብን ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች በማዋል በግልፅነትና ተጠያቂነትን ሊፈጸም ይገባል ያሉት ኢንጅነር ተፈራ አሰፋ ናቸው።


 

ሀገርና ህዝብን ለችግር እየዳረገ የሚገኘውን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድም ልዩ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል።

ወጣት ያብስራ ሽብሩ በምግብ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ህዝብ ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ መንግስት ህግ የማስፈጸም አቅሙን በማጠናከር ተጨባጭ መፍትሔ እንዲያመጣ ጠይቋል።


 

የኑሮ ውድነት ጫናውን በዘላቂነት ለመቀነስም በምርት አቅርቦት ላይ የተጀመሩ ተግባራት በአዲሱ የመንግስት የስራ ዘመን ትኩረት መሰጠት አለባቸው ብሏል።

በተጨማሪም  ለወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር ስራን በተለያየ አማራጭ አጠናክሮ መቀጠል የመንግስት የቤት ስራ እንደሆነም አንስቷል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም ህብረተሰቡም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም