የጀግናው ሠራዊታችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር ለጀማሪ መኮንኖች ልዩ አቅም የሚፈጥር ነው- ሰልጣኝ ዕጩ መኮንኖች - ኢዜአ አማርኛ
የጀግናው ሠራዊታችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር ለጀማሪ መኮንኖች ልዩ አቅም የሚፈጥር ነው- ሰልጣኝ ዕጩ መኮንኖች
ድሬዳዋ ፤ መስከረም 25 /2016(ኢዜአ)፡- የሀገር ሉዓላዊነትን እያስከበረ ባለው በጀግናው ሠራዊት ውስጥ ያለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር ለጀማሪ መኮንኖች ልዩ አቅምና መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን የሁርሶ የኮንቲጀንትና ዕጩ መኮንኖች ማስልጠኛ ማዕከል ሰልጣኝ ዕጩ መኮንኖች አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የሁርሶ የኮንቲጀንትና ዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ማዕከል በወታደራዊ ሙያ የመጀመሪያ የሆነውን የአመራርነት ስልጠና ላጠናቀቁ ዕጩ መኮንኖች የትከሻ ምልክት የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ትናንት መካሄዱ ይታወሳል።
አካዳሚው በወቅቱ እንዳስታወቀው፤ በየደረጃው የሚገኙ ወታደራዊ መኮንኖችን በብቃትና በጥራት በማፍራት የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ሰልጣኞቹ እንደገለጹት ፤ የሠራዊቱን ልዩ ፍቅርና አንድነት በመጠበቅ ሀገርን ለማሻገርና የህዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ለመስራት ዝግጁ ናቸው።
የቀደምት አባቶችና እናቶችን የጀግንነት ፈለግ በመከተል የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ደህንነት በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ እንደሚተጉም ተናግረዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትን እያስከበረ ባለው በጀግናው ሠራዊት ውስጥ ያለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር ለጀማሪ መኮንኖች ልዩ አቅምና መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን አስታውቀዋል።
ከስልጣኞቹ መካከል ዕጩ መኮንን ዑስማን ፈይሳ በሰጠው አስተያየት፤ በማዕከሉ እየቀሰመ ባለው ዕውቀትና ወታደራዊ ሳይንስ ጥበብ በመታገዝና ከበላይ ወታደራዊ አዛዦች ጋር በመቀናጀት የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ለማስከበር እንደተዘጋጀ ገልጿል።
በማዕከሉ ያለው ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ፍቅር ለጀማሪ መኮንኖች ልዩ ኃይልና መነቃቃት እንደሚፈጥር አመልክቶ፣ይህን ፍቅርና አንድነት በመጠበቅ ሀገርን ለማሻገርና የህዝብ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንተጋለን ብሏል።
" የሀገሬን ዳር ድንበርና የዜጎችን ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ህይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ" ያለው ደግሞ ሌላው ዕጩ መኮንን ጥሩሰው በላይ ነው።
ዕጩ መኮንን ዓለማየሁ ታደሰ በበኩሉ ፤ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር በቂ አካዳሚያዊና ወታደራዊ ስልጠና እየቀሰሙ መሆናቸውን ተናግሯል።
በቀጣይ የእናት ሀገሩን ዳር ድንበር ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ተመስገን አቦሴ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የዜጎችን ዘላቂ ሰላም ለማስከበር የሚያስችሉ ጀማሪ ወታደራዊ መኮንኖችን በጥራትና በብቃት የማፍራቱን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህብረ ብሔራዊ መሠረትን አፅንቶ ለሀገር ህልውና መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ስምና ዝና ለማጠልሸት የሚራወጡ ፀረ ልማትና ፀረ አንድነት ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበው፣ ሠራዊቱ መቼም ቢሆን ፅናቱን ጠብቆ ሀገርን ለማሻገር በቁርጠኝነት መትጋቱን ያጠናክራል ብለዋል።