ቀጥታ፡

በብዝሀ ማንነት ባጌጠችው አዲስ አበባ 5ኛውን የኢሬቻ ፎረም አከናውነናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2016 (ኢዜአ)፦ በብዝሀ ማንነት ባጌጠችው አዲስ አበባ 5ኛው የኢሬቻ ፎረም መከናወኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ተፈጥሮን ውብ አድርጎ የፈጠረውን ፈጣሪ የሚያመሰግንበትና የሚያከብርበት፣ የተጣላ ጸቡን በይቅርታ የሚሽርበት፣ የሰላም፣ የአብሮነት እና የአንድነት መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በአምስቱም በሮች የሚገቡ እንግዶችን ቤት ያፈራውን በመያዝ በፍቅር እየተቀበሉ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በተግባር በማሳየት አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኗን አስመስክረዋል ብለዋል።

ኢሬቻ የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት እና ገቢ በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋኦ እንዳለውና የከተማ አስተዳደሩም በዓሉን ለመታደም የመጡ በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን በክብር እያስተናገደ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢሬቻ ዕሴት ያልሆኑና መታየት የማይገባቸውን ድርጊቶች ከመፈጸም እየተቆጠብን በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነትና በድምቀት እንድናከብር ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።

አባገዳዎች ፣ሀደ ስንቄዎች፣ ፎሌዎች ፣ መላው አመራር ፣ የጸጥታ አካላት ፣የሰላም ሠራዊት አባላቶች እና መላው የከተማዋ ነዋሪ ለፎረሙ ላደረጉት ሁሉ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም