በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት በሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሪን በሚያሳጣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 30 ግለሠቦችና የተለያዩ መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት በሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሪን በሚያሳጣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 30 ግለሠቦችና የተለያዩ መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት በሚፈጥር እና የውጭ ምንዛሪን በሚያሳጣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል የተጠረጠሩ 30 ግለሠቦችና የተለያዩ መሣሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ::
በአዲስ አበባ፣ ሸገር ከተማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሃዋሳ እና ጂማ ከተማ በተደረገ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከ73 በላይ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ ማሣሪያ እና 30 ተጠርጣሪ ግለሠቦች እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በመተበበር እንዲሁም ከቴሌኮም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባለሙያዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ላለፉት ሦስት ወራት በቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ተዋንያን ላይ ጥብቅና ምስጢራዊ ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተቋማቱ ግኝቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን በላኩት የጋራ መገለጫ አመልክተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ የግለሠብ ቤቶችንና ግቢዎችን በመከራየት የማጭበርበሪያ መሣሪያዎችን ተጠቅመው ወንጀሉን ሢሰሩ መቆየታቸውን ያስታወቀው መግለጫው፤ ለዚሁ ሕገ ወጥ ተግባር ሲውሉ የነበሩ ከ200 ሺ በላይ የሳፋሪኮም እና ኢትዮቴሌኮም ሲም ካርዶች መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉ የማጭበርበሪያ ጌትዌይ መካከልም በአንድ ጊዜ 127 የኢትዮቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም ሲም ካርድ መያዝ የሚችል መሣሪያ መገኘቱንም ጠቁሟል፡፡ በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት የሚፈጸሙት የማጭበርበር ድርጊቶች ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣ የጠቆመው መግለጫው፤ ኢትዮቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ500 ሚልዮን በላይ ብር በዚህ ሕገ ወጥ ተግባር የተነሳ ማጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሕገ ወጥ ድርጊቱ በሀገር ደኅንነት ላይ ሥጋት የሚፈጥርም መሆኑን ያመለከተው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጋራ መግለጫ፤ በማጭበርበሪያ መሣሪያዎች የተነሳ በቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ጠቁሟል፡፡
መሣሪያዎቹ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሲሆን፤ ከኢትዮቴሌኮም ይሁን ከሳፋሪኮም ምንም እውቅና የሌላቸው ነገር ግን ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ሳፋሪኮም በዘረጋው ኔትወርክ ሳይሆን ራሳቸው በዘረጉት የማጭበርበሪያ ጌትዌይ ለደንበኞች የሚያቀርቡ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በማጭበርበሪያ መሣሪያው የሚፈጸመው ሕገወጥ ድርጊት ሀገራዊ ጥቅምን ከማሳጣትና የደኅንነት ሥጋት ከመደቀን ባሻገር የቴሌኮም ደንበኞች በሚፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ ጥራት ያለው የኔትዎርክ አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረጉን፤ በዚህም ደንበኞች በቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት እንዲማረሩና ሀገራዊ መረጋጋት እንዳይኖር አስተዋጽዖ ማበርከቱን መግለጫው አስታውቋል፡፡
በማጭበርበር ወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ ግለሠቦች ሰፊ ኔትዎርክ ያላቸው ሲሆን፤ ከአለም ዓቀፍ ተዋንያን እስከ ሀገር ውስጥ ቤት አከራይ ድረስ ትስስር መፍጠራቸውን የተቋማቱ የጋራ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የማጭበርበሪያ መሣሪያ ከጎረቤት ሀገራት በድንበር በኩል እስከ መሀል ከተማ ድረስ የሚቀባበሉ ደላሎች፣ በርካታ የኢትዮቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ሲም ካርድ እና ሞባይል ካርድ ለእነዚህ አጭበርባሪዎች የሚያደርሱ ተባባሪ ወንጀለኞች እንደሚገኙበት አመልክቷል፡፡
በተለይ ተጠርጣሪዎች መቀመጫቸውን ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ሀገራት ካደረጉ ዜጎች ጋር በመመሳጠር እና ተቀጥረው በመሥራት ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደተደረሰባቸው ጠቁሟል።
እንደ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጋራ መግለጫ፤ በኦፕሬሽኑ በተያዙት መሣሪያዎች እና በተጠርጣሪዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቀጣይ ምርመራውን አጠናክሮ በመቀጠል፤ በቀጣይ ለሕዝብ የማሳወቅ ሥራ የሚያከናውን ይሆናል፡፡
ሁሉም አካላት በሀገር፣ በዜጎች እና በተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱት እነዚህና ሌሎችም መሰል ወንጀሎች ከጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት እይታ እንደማይሰወሩ ተገንዝበው ከሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል መግለጫው።
ኅብረተሰቡም የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊቶች ከሚያደርሱት የኢኮኖሚ ኪሳራ በተጨማሪ በሀገር ደኅንነት ላይ የሚያስከትሉትን አደጋ በመገንዘብ በተመሳሳይ ወንጀል የሚሳተፉ ግለሠቦችና ተቋማት መኖራቸውን ጥርጣሬ ሲያድርበት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታና የሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማውን በማቅረብ ሕገወጦችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡