ለሕክምና የሚሆን ደም እጥረትን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ለሕክምና የሚሆን ደም እጥረትን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ ጥሪ ቀረበ
ሐረር ፤መስከረም 24/2016 (ኢዜአ):- ለሕክምና የሚሆን የደም እጥረትን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ የኢትዮጵያ የደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዓመታዊ ጉባዔውን በሐረር ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ እንደተናገሩት በ2015 በጀት ዓመት ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማንቀሳቀስ ወደ 353 ሺ ዩኒት የሚጠጋ ደም በአገር አቀፍ ደረጃ ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡
የተሰበሰበውን ደም ደህንነት በዘመናዊ የምርመራ ማሽን የመመርመር እና የደም ዓይነት ልየታ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ከአይን ባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለህክምና የሚሆን ደም፣ የደም ተዋፅኦ፤ የአይን ብሌን እና ሌሎች ህብረ ህዋስ ፍላጎት እና አቅርቦትን ከማመጣጠን አኳያ ውስንነት እንደሚታይም አመልክተዋል።
በተለይ የማህበረሰቡ አመለካከት ውስን መሆን፣ በአገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግርና እና ሌሎች ለእጥረቱ መከሰት ምክንያቶች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
''የደም ባንኮችን ለአክሬዲቴሽን በማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ መስራት ሌላው ትኩረት የሚሻ ተግባር መሆኑን ጠቁመው አግባብነት ያለው የደም አጠቃቀምን ለማበረታታት ከህክምና ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራትም ይገባል" ብለዋል፡፡
ለሕክምና የሚውል የደም እጥረትን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ ደም እንዲለግስ አቶ ሃብታሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደም ባንኮችም የአይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የሚገቡ ሰዎችን ቁጥር ለመጨመር በጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ዮኒስ በበኩላቸው በክልሉ ለህክምና አገልግሎት የሚውል ደም እና የደም ተዋጽኦ ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከበጎ ፈቃደኞች የሚሰበሰበው ደም እየተሻሻለ ቢገኝም አሁንም ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አለመቻሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ የደም ለጋሾችን ቁጥር በማሳደግና የደም ባንኩን አደረጃጀት በሰው ሃይልና በግብዓት በማደራጀት የተሻለ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሐረሪ ክልል በ2015 በጀት ዓመት 4800 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የፈውስ ህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር ኢማን ዘይዳን ናቸው።
በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ 8 ሺህ 526 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ በሶስት ወራት ውስጥ 1100 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱም አርቲስት ይገረም ደጀኔ እና አርቲስት ሸዊት ከበደ የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የክብር አምባሳደር ሆነዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የደም እና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት መማክርት አባላት፣ የክልል ጤና ቢሮ የፈውስና ተሃድሶ አገልግሎት ዳይሬክተሮችና የደም ባንክ ተጠሪዎች፣ የደም ለጋሾች ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።