ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁና ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወቅቱ የሚጠይቀውን ብቁና ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል አካዳሚ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለስድስት ወራት በመሠረታዊ ውትድርና ሙያ ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች አስመርቋል። 


 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ፤ የአየር ኃይል ተቋማዊ የለውጥ እርምጃ በመውሰድ ለውጤታማ የሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል። 

የአየር ኃይል አካዳሚም ዓለም የደረሰበትን የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ከግምት በማስገባት ወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ለምርቃት የበቁት መሠረታዊ ወታደሮችም ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ለገቡት ቃል-ኪዳን ተግባራዊነት ታላቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

በሰው ኃይል ግንባታው ወቅቱ  የሚጠይቀውን ብቁና ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባትም የነባሩን የአየር ኃይል አባላት ሙያዊ አቅም በማጎልበትና ለተሻለ ግዳጅ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በወታደራዊ ሥነ-ምግባር የታነጸ ተተኪ ሠራዊት መገንባት የሚያስችል የሰው ኃይል ለመፍጠር ውጤታማ ትምህርትና ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኃይል አካዳሚ ኮሎኔል ገዛኸኝ ነጋሽ፤ ተመራቂዎቹ የመከላከያ ሠራዊትን ባህልና እሴት የተላበሱ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

በቆይታቸውም ወታደራዊ ግዳጅ በታላቅ ኃላፊነት መወጣት የሚያስችል አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ወስደው መመረቃቸውን አረጋግጠዋል።

የአየር ኃይል አካዳሚ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ሻምበል ፈቃዱ ገለቱ፤ ተመራቂዎቹ በአየር ኃይል አካዳሚ ውትድርና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ቆይታቸውም ወታደር መሆን የሚያስችላቸውን የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲከታተሉ እንደቆዩ ተናግረዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት መሠረታዊ ወታደር ሲሳይ በዛብህና መሠረታዊ ወታደር ወይንሸት ግርማ፤ አገራቸውን በታላቅ ኃላፊነት ለማገልገል ለምርቃት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ሌላኛው መሠረታዊ ወታደር ደረሰ ቱጫ በበኩሉ፤ በቀጣይም አየር ኃይሉን ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ ተመራጭ ተቋም ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጿል። 

በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

በመርኃ-ግብሩ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ዓመት በበረራና ቴክኒሻን የሙያ ዘርፎች ትምህርትና ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ለሚገኙ ሰልጣኞች የትከሻ ምልክት (ፍላግ) የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።

በቆይታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ1ኛ፣ የ2ኛ፣ የ3ኛ ዓመት የበረራና ቴክኒሻን ተማሪዎች እንዲሁም መሠረታዊ ውትድርና ምሩቃን ሽልማት ተበርክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም