የሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻን በዓል ታዳሚዎች የጉዞ መስተጓጎል እንዳይኖር የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቷል - የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻን በዓል ታዳሚዎች የጉዞ መስተጓጎል እንዳይኖር የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቷል - የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ የሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻን በዓል ታዳሚዎች የጉዞ መስተጓጎል እንዳይኖር የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ቅድመ-ዝግጅት መጠናቀቁን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
የፊታችን መስከረም 26 እና 27 በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተማ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አከባበርን ተከትሎ በበዓሉ ታዳሚዎች እንቅስቃሴ የትራንስፖርት መጨናነቅ እንደሚጨምር ይታወቃል።
ሚኒስቴሩም የትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር እንዳይፈጠር ከኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ዝግጅት አድርጌያለሁ ብሏል።
በተለይም ለሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ አከባበር ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ ለሚያቀኑ የበዓሉ ታዳሚዎች በመዲናዋ በሚገኙ ስድስት መናኸሪያዎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋጀቱን ነው የገለፀው።
በዚህም በአዲስ ከተማ ትልቁና ትንሹ መናኸሪያ፣ አስኮ፣ አየር ጤና፣ ቃሊቲና ላምበረት በሚገኙ መናኸሪያዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ተዘጋጅቷል ብሏል።
ከመናኸሪያዎች በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ የተለያዩ የመነሻ ቦታዎች በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተዘጋጀም እንዲሁ።