ቀጥታ፡

ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር

አሶሳ ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ) ፡-ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ ሆራዛብ ከተማ በ282 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው የመጠጥ ውሃ እና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡


 

ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት በአገሪቷ ድርቅ ከሚያጠቃቸው አካባቢዎች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ አንዱ ነው፡፡

መንግስት በድርቅ በሚጠቁ አካባቢዎች የውሃ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ዛሬ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠለት የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትም የዚሁ አካል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የግንባታ ተቋራጭ ተለይቶ የግንባታ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው መግባት ጀምረዋል ብለዋል፡፡

''መንግስት የሚጀምራቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ ለፕሮጀክቱ አፈጻጸምም አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የክልሉ ህዝብ በአፈጻጸሙ የሚያጋጥሙ ክፍተቶች ካሉ ተገቢውን ክትትል በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ በክልሉ ያሉ የልማት ክፍተቶች በጥናት ተለይተዋል ብለዋል፡፡


 

የመጠጥ ውሃ፣ መንገድ፣ ስልክ የመሳሰሉት ጥናት ከተደረገባቸው መሰረተ ልማቶች መካከል መሆናቸውን ጠቁመው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር መሰረተ ልማቶቹን የማሟላት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ሊገነባ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የዛሬው ፕሮጀከት ዋነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

''የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፍ በክልሉ የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመፍታት ያግዛል'' ያሉት ደግሞ የክልሉ ውሃ እና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ሞርካ ናቸው፡፡

ቢሮው ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ህብረተሰቡን ከማስተባበር ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

በሚቀጥሉት 13 ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃው ፕሮጀክቱ ሶስት ከፍተኛ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች፣ 29 ቦኖዎች፣ 43 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር፣ አምስት መጻዳጃ ቤቶች በግንባታው ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ናቸው፡፡

የፕሮጀክቱ በጀት ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሆኑም በወቅቱ ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም