ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሀዋሳ፤መስከረም 24/2016 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ለአዲሱ ስርዓት ትምህርት ትግበራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ  መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ዮሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት በክልሉ ሰፊ ቅድመ  ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።

ክልሉ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት በ73 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው አሁን ላይ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ወደ ሙሉ ትግበራ መገባቱን አስታውቀዋል።

በተለይ በሥርዓተ ትምህርቱ መሠረት የተዘጋጁ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቶ ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ  የክልሉ መንግሥት በመደበው 346 ሚሊዬን ብር 1 ሚሊዬን 783 ሺህ ኮፒ የመፅሐፍት ህትመት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዘንድሮም ዓመት በተመሳሳይ በ346 ሚሊዬን ብር የቀሪ የትምህርት መፅሐፍት የህትመት ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በተለይ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚገኙ ተማሪዎች ቅድሚያ መጽሐፍት እንዲደርሳቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት  አቶ ሚሊዬን በህትመት ላይ የሚገኙት ሁሉም መፅሐፍት እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠቃለው እንደሚገቡም ገልጸዋል።

ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ያሉ ህጻናት የማንበብና የማስላት ክህሎታቸውን ለማዳበር የሚያስችሉ መፅሐፍትን ለማሳተም በመጀመሪያው ምዕራፍ የተመረጡ 145 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በፕሮጀክት መታቀፋቸውን ጠቅሰዋል።

ለፕሮጀክቱም 10 ሚሊዬን ብር ተበጅቶ 270 ሺህ የማጣቀሻ መፅሐፍት እንዲታተሙ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው በ2ኛው ምዕራፍ ደግሞ ለ346 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ በጀት ተበጅቶና መጽሐፍት ታትመው እየተሰራጩ እንደሚገኙም አውስተዋል።

ቀሪዎቹን 518 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማዕቀፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም አዲሱ ስርዓት ትምህርት በተመረጡ ሶስት ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ ዘንድሮ ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት እየተሰራ ነው ያሉት።

ይህም ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ ለህትመት እስከሚበቃ ድረስ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጁ የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች  በሶፍት ኮፒ በኮምፒውተሮች በማዳረስ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማሳለጥ እንደሚረዳ አስታውቀዋል።

ሌላኛው ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ማዕቀፍ ጋር የተያያዘው የትምህርት በሬዲዮ ሥርጭት መሆኑን ያነሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው በዚህ ረገድም 576 የሬድዮ ስክሪፕት ዝግጅት ተጠናቆ በቀረፃ ሂደት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የክልሉ ማህበረሰብ አጋርነቱን የገለጸበት አግባብ እንዳለ አንስተዋል።

ከሐምሌ 03 ቀን 2015 ጀምሮ ክልላዊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር 225 ሚሊዬን ብር ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመው በተገኘው ሀብትም በየደረጃው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በውሰጥ ቁሳቁስ ግብዓት የማደራጀትና የማጠናከር ሥራ መሰራቱን አመላክተዋል።

በሀዋሳ ከተማ የአላሙራ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዳዊት መኩሪያ በሰጡት አስተያየት ለአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አንዱና ወሳኝ በመሆኑ መሠረተ ልማቱን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ትምህርት ቤታችን ተማሪዎች ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መማራቸው ብቻውን በቂ ስላይደለ የዲጂታል ቤተ ሙከራ ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል ይህም የሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች መፅሐፍትና ማጣቀሻ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

በትምህርት ቤቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪ አሚና ሼይቾ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪ ማራናታ አበራ በሰጡት አስተያየት በትምህርት ቤቱ የሚገኘው የኮምፒውተር ማዕከል እውቀታችንን ለማዳበርና ውጤታችንን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለዋል።

በተለይ በየዝንባሌያችን ተመራማሪ እንድንሆን ከማነሳሳት ባለፈ ለመማር ማስተማሩ ሥራ መሳለጥ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘባቸውን  ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በመደበኛው መርሃ ግብር ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ። 

ከተጠቀሱት ተማሪዎች ከ231 ሺህ በላይ የሚሆኑት የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ባሉ የክፍል ደረጃዎች የሚማሩ መሆናቸውን ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም