ቀጥታ፡

ቦርዱ በተለያዩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የማጣራት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በተለያዩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የማጣራት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ቦርዱ የደረሰውን ጥቆማን መሰረት በማድረግ የመስክ ምልከታ ባደረገበት በቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ “አፖስቶ” ግቢ ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት የታሰረ ሰው እንደሌለ ማረጋገጡንም አስታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በሲዳማ ክልል የቀድሞ ደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ አፖስቶ ግቢ በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጓል።


 

የተጠቀሰው ቦታ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ ስር የሚካተት ባይሆንም ዜጎች እየታሰሩበት ነው በሚል ከተለያዩ ወገኖች ለቦርዱ ጥቆማ በመድረሱ በአካል ምልክታ መደረጉ ተገልጿል።

ቦርዱ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የደቡብ ክላስተር ዋና ክፍል፣ ከሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ከኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያይቷል።

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ነጃት ግርማ በዚሁ ወቅት፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰረ ምንም አይነት ግለሰብ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ አለመኖሩን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ከዚህ ቀደም ወደ ኮሌጁ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ባልተያያዘ መደበኛ የወንጀል ስጋት የተጠረጠሩ ከአዲስ አበባ ለተሃድሶ ስልጠና የመጡ ግለሰቦች እንደነበሩ የሚመለከታቸው አካላት ለቦርዱ መግለጻቸውን ዶክተር ነጃት ተናግረዋል።

ቦርዱ ባደረገው ማጣራትም በኮሌጁ ውስጥ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉም ሆነ ለስልጠና የገቡ ሰዎች እንደሌሉ በተጨባጭ ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎች መሰረት ቦርዱ በተለያዩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የመከታተልና የማጣራት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።


 

የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች በክልሉ ብሔር ተኮር እስር እየተፈጸመ እንደሆነ ተደርጎ የሚናፈሰው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።

በቀድሞ ደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚገኙት የሲዳማ ክልል የፖሊስ ማርሽ ባንድ አባላት ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውጭ ምንም አይነት ግለሰብ እንደሌለም ገልጸዋል።

የደቡብ ፖሊስ ማሰልጠኛ ኮሌጅ አካዳሚክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር ካሳሁን ተስፋዬ፤ ቀደም ሲል ከአዲስ አበባ ለተሃድሶ ስልጠና የመጡ ግለሰቦች እንደነበሩ አረጋግጠዋል።

ሆኖም አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ የግለሰቦች እስራት ተፈጽሟል በሚል የሚናፈሰው መረጃ ፈጽሞ ሀሰተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኮሌጁ ግቢ ውስጥ የነበሩት ግለሰቦች የተለያዬ ማንነት ያላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የመጡበት ዓላማም በወንጀል ታስረው ሳይሆን የግንዛቤ ስልጠና እንዲያገኙ ነው ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የደቡብ ክላስተር ዋና ክፍል ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አባይ ለማ ቦርዱ በስፍራው ተገኝቶ ላደረገው ማጣራት ምስጋና አቅርበዋል።

ይህም በሀሰተኛ መረጃ ምክንያት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ መደናገሮችን እንደሚያስወግድ ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም