የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር ከአባገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር ውይይት አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር ከአባገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር ውይይት አካሄደ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲከበር ከአባገዳዎችና ከሀደሲንቄዎች ጋር ውይይት አካሄደ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ለአባገዳዎችና ለሀደሲንቄዎች ገልፀዋል፡፡
በበዓሉ ላይ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት በዓል በመሆኑ ከዋዜማው ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የሆራ ፊንፊኔ እና በቢሾፍቱ ከተማ በሚከበረው የሆራ አርሳዲ ማጠናቀቂያ ድረስ ግብረ ኃይሉ ከአባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ የአዲስ ዓመትና የመስቀል ደመራ በዓላት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰላም እንደተከበሩ ሁሉ የኢሬቻ በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
ለዚህም ከመላ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲከበር እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሸነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ለአባገዳዎችና ለሀደሲንቄዎች አብራርተዋል።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ሁሉ ችግሮችን በመፍጠር የበዓሉን ድባብ ለማደብዘዝ የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸዋል።
"በሰላማዊ ትግል ያልተሳካላቸውና የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት በተለያዩ መንገድ ለማሳካት የሚፈልጉት ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል የሚያደርጉት እንቅስቃሴን መግታት ችለናል" ብለዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካካል አባገዳ ጎበና ሆላ የኢሬቻ በዓል ከፖለቲካና ከሃይማኖት ነፃ በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ የገዳ ሥርዓት ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች አቅፎ እና በባለቤትነት መንፈስ የበዓሉ ታዳሚዎችን ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ እንዲያስተናግድ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
“ወጥቶ ለመግባትና ወልዶ ለመሳም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው” ብለዋል።
በዓሉን ሊያደናቅፉ የሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አርማና አልባሳት፣ ስለታማ ነገሮችን፣ አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ የሚያወድስና ሌላውን ደግሞ የሚያንኳስሱ ዘፈኖችን ማሰማት ፈፅሞ እንደማይቻልም ጠቁመዋል።
ይህንን ክልከላ ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ እርምጃ በመውሰድ ለበዓሉ ስኬት እገዛ እንዲያደርግም አባገዳ ጎበና ጥሪ አቅርበዋል፡፡