በኢሉባቦር ዞን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ጠንካራ የጥራትና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው-- የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በኢሉባቦር ዞን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ጠንካራ የጥራትና የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው-- የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት
መቱ ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ በኢሉባቦር ዞን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡናን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ጠንካራ የጥራትና የቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አስጨናቂ አድማሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዞኑ ከፍተኛ የቡና ምርት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።
እንዲያም ሆኖ በዞኑ ከሚመረተው የቡና ምርት አንጻር ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው የሚጠበቀውን ያህል አይደለም ብለዋል።
በዞኑ ለቡና ጥራት መጓደል መንስኤ ከሆኑት መካከል ያልበሰለ ቡናን መልቀምና ቡናን መሬት ላይ ማድረቅ ዋናዎቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የቡና ነጋዴዎች የቡናን ጥራት እየፈተሹ ያለመግዛት እንዲሁም የቡና ምርት ሂደቱ ጥራትን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑን አክለዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ችግሩን ለመቅረፍ ከአርሶ አደሮችና ከቡና ነጋዴዎች ጋር በየጊዜው ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የግብርና ባለሙያዎች ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት በየደረጃው ከሚገኘው የቡና ጥራት ግብረ ኃይል ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመትም በዞኑ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበው 165 ሺህ ቶን ቡና ውስጥ 96 ቶኑን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከወዲሁ የጥራት ማስጠበቂያ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የቡና ጥራት ደረጃን በማስጠበቅ ከዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን ለማሳደግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማደግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
በዞኑ በቡና ንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩት መካከል አቶ ሐሰን ሲራጅ ''ስለቡና ጥራት ለብዙ ዓመታት የተወያየንበትና የመከርንበት ቢሆንም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አልመጣም'' ብለዋል።
ቡናን በጥራት ለማምረት የብዙ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚፈልግ ቢሆንም አምራቹ ግን ትልቁን ድርሻ ይይዛል ነው ያሉት።
በተለይም አርሶ አደሩ፣ የቡና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ተቀናጅተው ከሰሩ ለውጥ እንደሚመጣ ገልጸው እንደ ቡና ነጋዴ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
''አርሶ አደሩ ከለቀማ እስከ ማድረቅ ባለው ሂደት ለቡና ጥራት የሚሰጠው ትኩረት የቡናውን ዋጋ የሚወስን መሆኑን በውል ተገንዝቦ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ለማቅረብ መስራት አለበት'' ያሉት ደግሞ ሌላው በቡና ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ቡልቴሳ ሁንዱማ ናቸው።
የቡና ነጋዴዎች ቡናን ሲገበያዩ በጥራት መመረቱን፣ በአግባቡ መድረቁን አረጋግጠው በመግዛት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም መክረዋል።
ከዞኑ ቡና አምራች አርሶ አደሮች መካከል አቶ ታከለ ዲሳሳ በበኩላቸው የቡና ጥራት ጉዳይ በቀጥታ የዋጋ መጠንን የሚወስን በመሆኑ ለጥራቱ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የዞኑ ቡና አምራች አርሶ አደሮችም የቡና ጥራት መጓደል ጥቅማቸውን የሚቀንስ መሆኑን ተረድተው ቅድሚያ ለጥራት መስጠት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሰሞኑን "የቡና ምርት ጥራት ለጋራ ብልጽግናችን" በሚል ቃል የቡና ጥራት የንቅናቄ መድረክ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን እና በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ላይ ማካሄዱ ይታወሳል።
በመድረኮቹም ቡናን በብዛት እና በጥራት በማምረት አገሪቷ በአለም አቀፍ ደረጃ ከቡና ምርት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ሁሉም በቅንጅትና በመማማር መስራት እንዳለበት ተነስቷል።
በተለይም በአምራች አርሶ አደሩ ላይ የሚስተዋለውን የቡና ምርት የጥራት ችግርን ለመቅረፍ ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበርና ህጋዊነት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተመልክቷል።