አምስት ሚሊዮን ዜጎችን በንፁህ መጠጥ ውኃ፣ በአካባቢ ንጽህናና ጤና አጠባበቅ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
አምስት ሚሊዮን ዜጎችን በንፁህ መጠጥ ውኃ፣ በአካባቢ ንጽህናና ጤና አጠባበቅ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ ወተር ኤይድ ኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ዜጎችን በንፁህ መጠጥ ውኃ፣ በአካባቢ ንጽህናና ጤና አጠባበቅ ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ አደረገ።
ስትራቴጂክ ዕቅዱ ወተር ኤይድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ እስከ 2032 ለመተግበር ካዘጋጀው የ10 ዓመት ስትራቴጂ የተቀዳ መሆኑም ተገልጿል።
በዚህም መሰረት የአምስት ዓመቱ ሀገር አቀፍ ስትራቴጂ ከ2023 እስከ 2028 በኢትዮጵያ እንደሚተገበር ተመላክቷል።
ስትራቴጂው የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና ቀውሶችን በጋራ ለመከላከል በቁርጠኝነት መስራት ያስችላልም ተብሏል፡፡
ስትራቴጂው ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ አገልግሎቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማዳረስ ያለመ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፤ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የወተር ኤይድ የስራ ሃላፊዎችና ተጠቃሚዎች ተገኝተዋል፡፡
ወተር ኤይድ ኢትዮጵያ በግብረሰናይ ድርጅትነት ተመዝግቦ ስራ ከጀመረበት ከ1991 ዓ.ም ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስድስት ሚሊዮን ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል ተብሏል፡፡