ወጣቶች በመደመር እሳቤ አንድነታቸውን በማጥበቅ ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት አለባቸው- የኢትዮዽያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በመደመር እሳቤ አንድነታቸውን በማጥበቅ ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት አለባቸው- የኢትዮዽያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ ወጣቶች ከከፋፋይ አጀንዳዎች በመውጣት በመደመር እሳቤ አንድነታቸውን በማጠናከር ለኢትዮዽያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ገለፀ።
በመደመር እሳቤ ላይ ኢዜአ ያዘጋጀው አራተኛው ምእራፍ የውይይት መድረክ "መደመር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት" በሚል በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፣ "መደመርና ወጣቶች ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ ብልፅግና" በሚል የውይይት መነሻ ሃሳብ አቅርቧል።
በማብራሪያውም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በመፍጠር የተጀመሩ የልማት እቅዶች እንዲሳኩ ወጣቶች የላቀ ሚና ይጠበቅባቸዋል ብሏል።
አሁን ላይ ወጣቶች በዓለም እያደገ የመጣው የቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ ወጣቶች በአሉታዊና ተፅእኖዎች እንደሚፈተኑም ገልጿል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ወጣቶች መልካም ተሞክሮዎችን በመውሰድ በመደመር እሳቤ ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና መስራት አለባቸው ብሏል።
ሀገር በቀል እውቀትና ክህሎቶችን በማዳበርና አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲሰሩም ጠይቋል።
በመሆኑም ወጣቶች ከከፋፋይ አጀንዳዎች በመውጣት በመደመር እሳቤ በአንድነት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልፅግና ሊሰሩ ይገባል ነው ያለው።
ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀቶችን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የምትመራበት ሁነኛ መንገድ በማድረግና እሳቤው ለትውልድ እንዲተላለፍም “መደመር”፣ “የመደመር መንገድ” እና “የመደመር ትውልድ “ የሚሉ መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል።