የመደመር እሳቤ በብዝሃ ማንነት ውስጥ ያሉ አቅሞችን ለጋራ ልማት እንዲውሉ እድል የፈጠረ ነው - አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር እሳቤ በብዝሃ ማንነት ውስጥ ያሉ አቅሞችን ለጋራ ልማት እንዲውሉ እድል የፈጠረ ነው - አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤ በብዝሃ ማንነት ውስጥ ያሉ አቅሞች ለጋራ ልማት እንዲውሉ እድል የፈጠረ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ይስሃቅ አብዱልቃድር ተናገሩ።
"መደመር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት" በሚል ኢዜአ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ይስሃቅ አብዱልቃድር፤ በመድረኩ“ መደመር ለጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና አዎንታዊ ሰላም” በሚል የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ብዝሃ ማንነት አገርን በተደመረ አቅም ለመገንባት ትልቅ እድል መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የመንግስት ስርዓቶች በኢትዮጵያ ያለውን ህብረ ብሔራዊነት የአገር አቅም አድርጎ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው አስታውሰዋል።
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነቶች ውስጥ ያሉ አቅሞችን ለሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲሁም ለአገራዊ ልማት ማዋል ተችሏል ነው ያሉት።
በተለይ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ሁሉም እኩል ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዚህ ረገድ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
ክልሉ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እኩል ተሳትፎ በማድረግ ለአገረ መንግስት ግንባታ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በብዝሃ ማንነት ውስጥ ያሉ አቅሞችን ለጋራ ልማት እየዋሉ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።