ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው በሙሉ አቅማቸው ስራ ያልጀመሩ ባለሀብቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዳማ ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ያልገቡ ባለሁብቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ኢንዱስትሪ ፓርኩ አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጉልላት አበበ እንደገለፁት በፓርኩ 13 የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ ነው።

በፓርኩ እያለሙ ካሉ 13 ባለሀብቶች 7ቱ በ2015 ዓ.ም የገቡ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ጉልላት በበጀት ዓመቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ከመቀበል አንፃር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በፓርኩ ከገቡት 13 ባለሀብቶች መካከል 5 የሚሆኑት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ገብተው ከ8 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።

ወደ ፓርኩ የገቡና እስከ አሁን በሙሉ አቅማቸው ስራ ያልጀመሩ 7 ባለሀብቶች ወደ ተሟላ አምራችነት ለማስገባት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፓርኩ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላኩት ምርቶች 45 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ  ማስገኘቱን የገለፁት አቶ ጉልላት በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት ታቅዷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም ከውጭ ይገባ የነበረውን 600 ሚሊዮን ብር ግምት ያለውን የማኑፋክቸሪንግና ጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።

በፓርኩ ውስጥ የገቡ ባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ ማምረት ሲጀምሩ 15 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በማነቃቃትና በመደገፍ ረገድ የድርሻውን እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካትና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ረገድ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በፓርኮቹ 100 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፈጠሩም ባለፈ 113 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮች ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህም ሀገሪቷ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ እያገኘች ያለችው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ 50 የሚሆኑ የውጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ በተገነቡ ሼዶች መግባታቸውን ተናግረዋል።

በሙሉ አቅማቸው ስራ ላይ ከሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ ባሕርዳር፣ ጅማና ሰመራ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በባለሀብቶች ለማስያዝ በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም