ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት እውን እንዲሆን ያደረገ የፍትሃዊነት መንገድ ነው - አቶ አሻድሊ ሃሰን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2016(ኢዜአ)፦ የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት እውን እንዲሆን ያደረገ የፍትሃዊነት መንገድ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር አሻድሊ  ሀሰን ተናገሩ።

"መደመር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት" በሚል ኢዜአ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የክልሉና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ  የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ታድመዋል።

የፓናል ውይይቱ የመደመር ጉዞ በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ በተለያዩ ከተሞች እያካሄደ ያለው የውይይት መድረክ አካል ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያዊያን በረዥም ጊዜ የአብሮነት ታሪካቸው በተደመረ አቅም ነጻነቷ የተጠበቀ አገር ለትውልዱ ማስረከብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎም ኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀቶችን መሰረት ባደረገው የመደመር እሳቤ እየተመራች በርካታ ድሎችን አስመዝግባለች ነው ያሉት።

ለአብነትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተገነባ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያዊያን የመደመር አቅም ማሳያ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የመደመር እሳቤ በሌሎች የፓለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ መስኮች በርካታ ድሎች እንዲመዘገቡ አድርጓል ነው ያሉት።


 

በተለይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ አጋር ክልል በሚል ስያሜ ሲጠሩ የነበሩ የዳር ተመልካች ክልሎችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ያመጣ እሳቤ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ አሳታፊ የፖለቲካ ስርዓት እውን እንዲሆን ያደረገ የፍትሃዊነት መንገድ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ውስጥ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የአገር ህልውናን የማጽናት መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የመድረኩ  ዋነኛ ዓላማ በመደመር እሳቤ ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።


 

መድረኩ የኢትዮጵያዊያን የመደመር ውጤት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መካሄዱ  ልዩ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ኢዜአ ከአሁን በፊት በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱና ጅግጅጋ ከተሞች መሰል መድረኮችን ማካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም