ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የሰው ሃይል ያስፈልጋል- የዞኑ ግብርና መምሪያ

መተማ ፤ መስከረም 24 ቀን 2016 (ኢዜአ) ፡-  በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰሊጥን ጨምሮ ሌሎች የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የሰው ሃይል  እንደሚያስፈልግ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የደረሰ ሰብልን ከብክነት በፀዳ መልኩ ለመሰብሰብ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ያስፈልጋል።

ባለፈው ዓመት ከ400 ሺህ በላይ የሰው ኃይል በሰብል ስብሰባው መሳተፉን አስታውሰው፤ በ2015/2016 የምርት ዘመን የተሸፈነው ሰብል ካለፈው የተሻለ በመሆኑ በርከት ያለ ሰራተኛ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዞኑ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 160 ሺህ 600 ሄክታሩ ሰሊጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ሰሊጥን ጨምሮ ሌሎች የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የሰው ሃይል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ እስካሁን 300 ሺህ የጉልበት ሰራተኞች በሰብል ስብሰባ ስራው መሳተፍ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

የሰብል ስብሰባው አፋጣኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰው ሀይል በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ የገለፁት ባለሙያው ፤ አሁንም ወደ አካባቢው በመምጣት በሰብል ስብሰባው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሰራተኞቹ በቂ መጠለያና የምግብ አቅርቦት መኖሩን በእርሻ ልማት ጣቢያዎች ምልከታ በማድረግ መረጋገጡንና ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚመጡ በቂ ትራንስፖርት መመቻቸቱን አስታወቀዋል።

በቋራ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ተሾመ ይቴ እንዳሉት፤በክረምቱ ወቅትከ550 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ችለዋል።

ካለሙት መሬትም 250 ሄክታሩ ሰሊጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰሊጥ አንዴ ከደረሰ በቀናት ጊዜ ውስጥ በቀላሉ ሊፈስ የሚችል ሰብል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰሊጥን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን ለመሰብሰብ 3 ሺህ ሰራተኞች እንደሚያስፈልጓቸውና እስካሁን አንድ ሺህ ሰራተኛ ማሳተፍ እንደቻሉ ገልፀዋል።

በምርት ዘመኑ 20 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት መቻላቸውን የገለፁት ደግሞ በመተማ ወረዳ ሽመል ጋራ ቀበሌ አርሶ አደር ጌጡ አጣናው ናቸው።

ለስብሰባ ስራው ከ20 በላይ ሰራተኛ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የቤተሰቦቻቸውን ጉልበት በመጠቀም መሰብሰብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እየደረሰ ያለው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ተጨማሪ ሰራተኛ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኽሩ ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬትም ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም